የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤውን ማጠናቀቂያ አስመልክቶ ንግግር አድርገዋል።
ዋና ኮሚሽነሩ በንግግራቸው የኢትዮጵያን ችግሮች ለመፍታት ብቸኛው መንገድ ውይይት እና ምክክር መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል።
ላለፉት 46 ቀናት አራት ሺህ ተሳታፊዎች በልዩ ልዩ አጀንዳዎች ላይ ሲመክሩ መቆየታቸውን ያስታወሱት ዋና ኮሚሽነሩ፣ ይህ ታሪካዊ ጉባኤ "የእኔነት" ሳይሆን "የእኛነት" የጋራ ራዕይ ጎልቶ የወጣበትና ኢትዮጵያውያን መፋቀር እና መቀራረብ ምን እንደሆነ በተግባር ያሳዩበት መሆኑን ገልጸዋል።
በሀገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ይህን ያህል ቁጥር ያለው ተሳታፊ አርሶ አደሩን፣ አርብቶ አደሩን እና የተገፉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ጨምሮ ከሁሉም አካባቢዎች ተውጣጥቶ፣ በአስቸጋሪው የክረምት እና የዘር ወቅት ሳይሰለች ለረጅም ቀናት መቆየቱ የጉባኤው ትልቁ ድል መሆኑን ፕሮፌሰር መስፍን አብራርተዋል።
በሂደቱም ልዩነቶች፣ ሙግቶች እና የሎጂስቲክስ ፈተናዎች ቢኖሩም ተሳታፊው ኢትዮጵያን ማዕከል አድርጎ በመወያየቱ እና በመደማመጡ የተሳካ ውጤት ላይ መድረስ መቻሉን በደስታ ተናግረዋል።
ምክክር በአንድ ጀንበር ተጀምሮ የሚያልቅ ሂደት እንዳልሆነ የጠቆሙት ዋና ኮሚሽነሩ፣ በጉባኤው የተለዩት አጀንዳዎች እና ውሳኔዎች በቀጣይ ወደየክልሎች እና ከተማ መስተዳድሮች ተልከው የክልል አቀፍ ውይይቶች እንደሚቀጥሉበት አሳውቀዋል።
አክለውም ከተነጋገርን ማናቸውንም ችግሮቻችንን መፍታት እንደምንችል ገልጸው፣ በመሳሪያ ምንጊዜም አሸናፊ መሆን እንደማይቻል እና እውነተኛ አሸናፊነት የሚረጋገጠው በጋራ ማሸነፍ ሲቻል ብቻ መሆኑን አውስተዋል።
በተጨማሪም ፕሮፌሰር መስፍን በቅርቡ ሀገር ጥለው ስለመውጣታቸው ተሰራጭቶ የነበረውን የተሳሳተ መረጃ በተመለከተ በሰጡት ምላሽ፣ ከሀገራቸው የመሸሽም ሆነ የመኮብለል ዓላማ እንደሌላቸው አረጋግጠዋል። በወጣትነት ዕድሜያቸው ሀገር ጥለው የመውጣት ሰፊ ዕድል እያላቸው በሀገራቸው መቆየታቸውን በማስታወስ፣ በቀረችው ዕድሜያቸውም ከኢትዮጵያ እንደማይወጡ ለተሳታፊዎች ቃል ገብተዋል።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: