Search

ልዩነቶችን በሠለጠነ መንገድ የመፍታት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ተከፍቷል፦ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረ ሥላሴ

ቅዳሜ ነሐሴ 16, 2018 118

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረ ሥላሴ ታሪካዊው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በስኬት መጠናቀቁን አስመልክተው ባደረጉት የማጠቃለያ ንግግር፣ ጉባኤው በኢትዮጵያ የፖለቲካ እና ማኅበራዊ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ያጋጠሟቸውን ታሪካዊ ስብራቶች፣ ጥልቅ አለመግባባቶች እና የሐሳብ ልዩነቶች በኃይል እና በመገፋፋት ሳይሆን በመደማመጥ እንዲሁም በጋራ ጥበብ መፍታት እንደሚችሉ በተግባር ያረጋገጡበት አዲስ የፖለቲካ ባሕል መፈጠሩንም አብስረዋል።

አሳታፊ እና አካታች በሆነው በዚህ ታላቅ መድረክ ላይ፣ ከአራቱም የሀገር ማዕዘናት የተውጣጡ አራት ሺህ የሚሆኑ ተመካካሪዎች መሳተፋቸውን ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ አስታውሰዋል።

ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የቀድሞ ታጣቂዎች፣ የዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የመንግሥት አካላት እና ታዋቂ ሰዎች በአንድነት የተሰባሰቡበት ይህ መድረክ የመላው ኢትዮጵያውያን እውነተኛ የውይይት ማዕከል መሆን መቻሉን አብራርተዋል።

ከሐምሌ 8 ቀን 2018 . ጀምሮ በተካሄደው በዚህ ጉባኤ፣ ኢትዮጵያን ወደፊት ለማሻገር እና ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት በሚያስችሉ ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ ጥልቅ ምክክር መደረጉ ተገልጿል።

ተሳታፊዎቹ በሀገር ግንባታ፣ በመንግሥት አወቃቀር እና ቅርጽ፣ በፌዴራል ከተሞች፣ በሃይማኖት፣ በተቋማት ግንባታ፣ በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች፣ በሰላም ግንባታ እንዲሁም በሙስና እና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ዙሪያ በስፋት መምከራቸውን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት አመልክተዋል።

በእነዚህ ዐበይት አጀንዳዎች ላይ የተደረገው ምክክር ቀላል እንዳልነበረ እና ጥልቅ የሐሳብ ልዩነቶች መስተዋላቸውን የጠቆሙት ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ፣ የጉባኤው ትልቁ ስኬት በልዩነቶች ውስጥም ቢሆን እርስ በርስ መደማመጥ፣ መከባበር እና ለሀገር የተሻለ መፍትሔ በጋራ መፈለግ መቻሉ ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

በማጠቃለያቸውም፣ ተመካካሪዎቹ ሐሳባቸውን በነጻነት በመግለጽ ኢትዮጵያን አሁን ካለችበት ፈተና አውጥተው ወደተሻለ ምዕራፍ የሚያሻግሩ የላቁ ምክረ ሐሳቦችን በማመንጨታቸው እንዲሁም ለሀገራቸው ላሳዩት ከፍተኛ ቁርጠኝነት ላቅ ያለ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በለሚ ታደሰ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: