የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል ለ45ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን "ፅናት ኮርስ መሰረታዊ ኮማንዶዎችን" በዛሬው ዕለት አስመርቋል።
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ባስተላለፉት መልዕክት የመከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያ መከታ ነው ብለዋል።
"የባዕዳን ተላላኪዎች ጠመንጃ ሀገር ያፈርሳል" ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እኛ ደግሞ እየሰራን ያለነው ሀገር ለማፍረስ የሚተጉ ፅንፈኛና ነውጠኞችን መመከት ነው ብለዋል።
የአየር ወለድና ኮማንዶ ኃይል በአካል ብቃቱ፣ በፅናቱና በከፍተኛ ወታደራዊ እውቀቱ የውጊያ አቅጣጫ ቀያሪ ኃይል በመሆኑ ከውጭና ከውስጥ የተቃጡ ወረራዎችንና ግጭቶችን በመመከት በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ፈተናዎች ውስጥ አልፎ ሀገራዊ አደራውን በብቃት መወጣቱን ገልፀዋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን ከሰማይ የመርዝ ዝናብ እየዘነበባቸው በጎራዴና በዲሞፍተር ተዋግተው ያቆዩልንን ሀገር ዛሬ ከቀኝ ገዢዎች ባልተናነሠ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ግኝቶችን ታጥቀንና የሠው ኪሳራ ቀንሰን በነበልባል አቅም የምንዋጋበት ዘመን ላይ እንገኛለን ብለዋል።
የእነኛን ጀግኖች ቃል ለመጠበቅና የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ዛሬም በተጠንቀቅ እንገኛለን ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የዛሬ ተመራቂዎች ምን ያህል እልህ አስጨራሽ ትንቅንቅ አድርገው ስልጠናቸውን እንዳጠናቀቁ በተመለከቱት ገለፃ መረዳታቸውን አንስተዋል።
የኮማንዶ ስልጠና ከቀላል ወደ ከባድ ከከባድ ወደ ውስብስብ የሚሻገርና ከውትድርና ወደ ላቀ ውትድርና ሽግግር ሂደቱን እንደ ስያሜያቸው በፅናት ተሻግረው ሀገራቸው እና ህዝባቸው የሠጣቸውን ተልዕኮ በቁርጠኝነት መወጣት እንዳለባቸው አደራ ሰጥተዋል።
ተመራቂዎቹ በእሳት ተፈትነው የወጡ፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በታማኝነትና በቁርጠኝነት ማስከበር የሚችሉ ዝግጁ ኃይል በመሆን ከነባሩ የኮማንዶ አባላት ጋር በመቀላቀል የቀደመ መለያ የሆነውን ጀግንነት እንዲያስጠብቁ ከጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ አደራ ተሰጥቷቸዋል።
በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላን ጨምሮ፣ ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል አበባው ታደሰ፣ የመከላከያ የተኩስ አመራር ኃላፊ ጄኔራል አለምሸት ደግፌ፣ የመከላከያ ሥልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ጄኔራል ይመር መኮነን፣ የመከላከያ መሃንዲስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ጄኔራል ደስታ አብ የአዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ፣ የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ፣ የክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደሮች ጄኔራል መኮንኖች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: