የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ሒደት ገና ከጅምሩ፣ ሐሳቡ ተጸንሶ ወደ ትግበራ ከገባበት ቅጽበት አንስቶ፣ እያንዳንዱን እርምጃ በድል እያጠናቀቀ የመጣ ታላቅ የትውልድ ስኬት ነው።
"ኢትዮጵያውያን በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው መመካከር አይችሉም፤ ቋንቋቸው የጠመንጃ አፈሙዝ ብቻ ነው" የሚለውን የተሳሳተ እና የቆየ ትርክት ለመስበር የተጀመረው ይህ ብሔራዊ ጉዞ፣ በመንገዱ ላይ ያጋጠሙትን እልፍ መሰናክሎች ጥሶ ማለፉ በራሱ ወደር የለሽ ድል ነው።
የዚህን ሒደት ፈታኝነት እና የተደረገበትን ርብርብ ለመረዳት፣ ልክ በኢትዮጵያ የውኃ ሀብት ላይ ሲፈጸም የነበረውን የታሪክ ደባ ማስታወስ በቂ ነው።
ኢትዮጵያ የራሷን የተፈጥሮ ጸጋ ተጠቅማ፣ በተለይም በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ፣ ከድህነት እንዳትወጣ እና እንዳትለማ የውጭ ጠላቶች እና ታሪካዊ ባላንጣዎች ያልፈነቀሉት ድንጋይ፣ ያልሸረቡት ሴራ እንዳልነበረ ሁሉ፤ በሀገራዊ የምክክር ሒደቱም ላይ ተመሳሳይ እና እጅግ የተቀነባበረ ፈተና ተጋርጦበት ነበር።
"ኢትዮጵያውያን ከተመካከሩ፣ ከተደማመጡ እና ከተግባቡ፤ የውስጥ ልዩነታቸውን በሰላማዊ መንገድ ፈትተው የማይናወጥ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ይገነባሉ" የሚል ከባድ ስጋት ያደረባቸው ኃይሎች፣ ሒደቱን ገና በእንጭጩ ለማኮላሸት ያልቆፈሩት ጉድጓድ አልነበረም።
ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ተከፋፍለው፣ ተቃቅረው እና ልዩነታቸውን እያሰፉ እንዲኖሩ የሚሹ አካላት፣ የምክክር ሒደቱ እንዲከሽፍ እና የጋራ መግባባት ፈጽሞ እንዳይፈጠር ከፍተኛ የሥነ ልቦና ጦርነት ከፍተው ነበር። የተሳሳቱ መረጃዎችን በማሠራጨት፣ ጥርጣሬን በመዝራት እና በኅብረተሰቡ ውስጥ ተስፋ መቁረጥን በማስረጽ፣ ሀገራዊ ምክክሩ ወደሚቀጥለው ምዕራፍ እንዳይሸጋገር እልህ አስጨራሽ የሴራ ድሮችን ሸርበዋል።
ሐሳቡ መነሻ ላይ ሲቀርብ ጀምሮ የነበረውን ከባድ የጥርጣሬ ዶፍ እና ኃይለኛ የትችት ርጅብኝ ማስታወስ፣ የሒደቱን አስቸጋሪነት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የፖለቲካ ልሂቃኑ ሳይቀሩ ሒደቱ የትም አይደርስም በማለት ተስፋ አስቆራጭ ትንበያዎችን ሲያዘንቡበት ነበር።
ይሁን እንጂ፣ ይህ ሀገራዊ የምክክር ሒደት የጠላትን መዋርት፣ የተወረወረበትን የጥፋት ጦርና ቀስት ሁሉ አክሽፎ፣ አፍራሽ ሴራዎችን በጥሶ በድል አድማስ ላይ ቆሟል። ይህ ጉዞ እጅግ ታላቅ ታሪካዊ ድል ነው።
ጠላቶች "ይከሽፋል፣ ይበተናል፣ እርስ በርሳቸው ይጣላሉ" ሲሉ፣ ሒደቱ ግን የኢትዮጵያውያንን ልብ በየአካባቢው እያቀራረበ፣ ልዩነቶችን እያጠበ፣ እና ሐሳቦችን ወደ አንድ ጠንካራ ማዕከል እየሰበሰበ መጣ። እያንዳንዱ የተካሄደ የውይይት መድረክ፣ እያንዳንዱ የተሰበሰበ ሐሳብ፣ ኢትዮጵያውያን በገዛ ጉዳያቸው ላይ በብስለት የመወያየት አቅም እንዳላቸው ያረጋገጠ የተግባር ድል ነበር።
ይህ ስኬት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አዲስ ብሩህ ምዕራፍ የከፈተ ነው። ለዘመናት የቆየውን፣ ሀገራዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮችን በጠመንጃ እና በኃይል ብቻ የመፍታት አውዳሚ አባዜ በይፋ ያከተመበት ታላቅ የታሪክ መታጠፊያ ነው።
"እኔ ብቻ ነኝ የማውቅልህ"፣ "እኔ እችላለሁ አንተ አትችልም" የሚሉትን አግላይ እና ጽንፈኛ የፖለቲካ ዕሳቤዎች አሸንፎ፣ በምትኩ የመደማመጥን፣ የመቻቻልን እና የወል እውነትን የማዋለድ የሠለጠነ ባሕል የገነባ ክቡር ምዕራፍ ነው። ጦርነት እና ግጭት ብቻ መፍትሔ ከሚመስልበት ጨለማ ዘመን፣ ኢትዮጵያውያን ዛሬ በድል ወጥተዋል።
ስለሆነም፣ ኢትዮጵያውያን የተደቀነባቸውን የሴራ ጋሬጣ ሁሉ ጥሰው፣ በሠለጠነ ውይይት እና ምክክር የተሻገሩበት ይህ አዲስ ምዕራፍ በሚገባ ሊዘከር እና ሊከበር ይገባል።
ይህ በታሪክ ማኅደር ውስጥ በወርቅ ቀለም ሊጻፍ እና ለቀጣዩ ትውልድ በትምህርትነት ሊተላለፍ የሚገባው ሕያው የድል ገድል ነው። በብዙ ድካም እና ጽናት፣ የጠመንጃ አፈሙዝ ታጥፎ የውይይት ጠረጴዛ የሞቀበት ይህ ታላቅ የምክክር ድል፣ የነገዋ ጠንካራ፣ የተረጋጋችና በልጆቿ አንድነት የበለጸገች ኢትዮጵያ ጽኑ መሠረት ሆኖ ለዘላለም ይኖራል! የጥፋት ሴራዎች ከሸፉ፤ ኢትዮጵያውያን ተመካክረው ታላቅ ድል አደረጉ!
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: