Search

ታሪክ በወርቅ ቀለም ሲጻፍ፡ የኢትዮጵያ የውይይት ድል እና የመጪው ትውልድ ኩራት

ቅዳሜ ነሐሴ 16, 2018 135

ለዘመናት የፖለቲካ ልዩነቶቿን በኃይል እና በጠመንጃ አፈሙዝ ስትፈታ የኖረችው ኢትዮጵያ፣ ዛሬ ታሪካዊ የለውጥ ምዕራፍ ላይ ቆማለች።

የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው በስኬት መጠናቀቁ ኢትዮጵያውያን ከዜሮ-ድምር የፖለቲካ ፍልሚያ ወጥተው በምክንያታዊነት እና በጠረጴዛ ዙሪያ መወያየት መቻላቸውን ያረጋገጠ ታላቅ ብሔራዊ ድል ነው።

ይህ ኩነት የፖለቲካ ኃይሎች ጥያቄዎቻቸውን በጉልበት ሳይሆን በሀሳብ የበላይነት ብቻ የሚያስመልሱበትን አዲስ ዴሞክራሲያዊ ባህል ያሰረጸ አንጸባራቂ የታሪክ አጋጣሚ ነው።

ከመላው ኢትዮጵያ የተወከሉ 4 ሺህ ተመካካሪዎችን በአንድ አዳራሽ በማሰባሰብ የተካሄደው ጥልቅ ውይይት በተጨባጭ ማስረጃዎች እና በሰነድ በተደገፉ የመፍትሔ ሀሳቦች ታጅቦ የኢትዮጵያን አሸናፊነት በተግባር አረጋግጧል።

ተመካካሪዎቹ የቡድን እና አካባቢያዊ ስሜቶችን ወደ ጎን በመተው የጋራ እና ዘላቂ ጥቅምን በማስቀደም 8 ዐበይት አጀንዳዎች ላይ በጥልቀት መክረዋል።

በዚህም ለዓመታት የከፋ የፖለቲካ ውጥረት ምንጭ ሆነው በቆዩ ጉዳዮች ላይ ታሪካዊ ስምምነቶች ተመዝግበዋል።

በስምንቱ ዐበይት አጀንዳዎች ማዕቀፍ ውስጥ የጋራ መግባባት ላይ የተደረሰባቸው አጀንዳዎች እንዳሉ ሆነው፣ በተመካካሪዎች የተነሱ ሁሉም ሀሳቦች ተሰንደው ለፖሊሲ ግብዓት እንዲሆኑ መቀመጣቸው ለኢትዮጵያ ሌላኛው ትልቅ የሀብት ምንጭ ነው።

ይህ ውስጣዊ አንድነት እና መግባባት ኢትዮጵያ በቀጣናውም ሆነ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተሰሚነት እና ጂኦ-ፖለቲካዊ አቅም በእጅጉ የሚያጎላው ነው።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ይህን ፈታኝ ሂደት በገለልተኝነት፣ በብቃት እና በከፍተኛ ሙያዊ ጥራት በመምራት ላስመዘገበው ስኬት በታሪክ ማኅደር ውስጥ ትልቅ ቦታ ይዟል።

ይህ የምክክር መድረክ ማጠናቀቂያ ሳይሆን የአዲስ ጅማሮ ማብሰሪያ ነው። አጀንዳዎችን ከታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል በማሰባሰብ እና በነፃነት በመወያየት የጋራ ውሳኔ ላይ መድረስ መቻሉ ኢትዮጵያውያን በገዛ እጃቸው ዕጣ ፈንታቸውን መወሰን እንደሚችሉ አረጋግጧል።

የዛሬው ትውልድ የጥፋት ሳይሆን የማነጽ፣ የመለያየት ሳይሆን የአንድነት ባለቤት መሆኑን በተግባር አስመስክሯል።

በዚህም ምክክሩ ኢትዮጵያ ማሸነፏን ያረጋገጠችበት ታሪካዊ ሂደት ሆኖ የዛሬውን ትውልድ አስተዋጽኦም በወርቅ ቀለም ጽፎ በስኬት ተጠናቅቋል።

በለሚ ታደሰ  

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: