Search

የምህረት፣ የሰላም እና የመተሳሰብ ብርሃን፤ ታላቁ የነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) 1501ኛው መውሊድ በድምቀት

ማክሰኞ ነሐሴ 19, 2018 38

በየዓመቱ በረቢዑል አወል ወር በታላቅ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ሥነ-ሥርዓት የሚከበረው የነቢዩ ሙሐመድ (..) የልደት ቀን (መውሊድ) የነቢዩን መወለድ ከመዘከር ባሻገር የሕይወት ጉዟቸውን፣ ሰብአዊ እሴቶቻቸውን እንዲሁም የመተሳሰብና የሰላም አስተምህሮዎቻቸውን በመዘከር በድምቀት የሚከበር ታላቅ በዓል ነው።

በዚህ የተባረከ በዓል የእምነቱ ተከታዮች ከታላቁ መልዕክተኛ (..) ጋር ያላቸውን መንፈሳዊ ቅርበት ያድሳሉ፤ የፍቅርና የርህራሔ ታሪካቸውንም ለተተኪው ትውልድ ያስተላልፋሉ።

​"መውሊድ" የሚለው የአረብኛ ቃል በቀጥታ "ልደት" የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን፣ በሒጅራ አቆጣጠር በረቢዑል አወል ወር 12ኛው ቀን የተወለዱበትን ዕለት ለማሰብ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ በጋራ የሚያከብረው በዓል ነው።

መውሊድ በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በሀገራችን ኢትዮጵያ ሲከበር የምህረት፣ የፍቅር፣ የርህራሔ፣ የለጋስነት፣ የፍትሕና የሰላም እሴቶችን ለማጠናከር እንደ ታላቅ መልካም አጋጣሚ ይወሰዳል።

በዕለቱም በመስጂዶችና በማኅበረሰብ ስብሰባዎች የጋራ ዱዓዕ ይደረጋል፤ የነቢዩን (..) ሕይወትና መልካም ሥነ-ምግባር የሚያስታውሱ ድርሳናትና ኪታቦች ይቀርባሉ።

የሐዲስ ትምህርቶች እየተነበቡ፣ በሕብረት ዜማና በመንዙማ በደመቀ ሁኔታ የሚከበር ሲሆን፤ የእምነቱ አባቶችና ምዕመናንም ስለ ሀገራችን ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት በጋራ ይጸልያሉ።

ኢትዮጵያ ከቀደምት የእስልምና ታሪክና ከታላቁ ነቢይ ባልደረቦች (ሶሐቦች) ጋር ጥልቅ ትስስር ያላት ሀገር እንደመሆኗ፣ መውሊድ ከሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓትነቱ ባሻገር ከማኅበራዊና ባህላዊ እሴቶቻችን ጋር አብሮ የሰረፀ ታሪካዊ በዓል ነው።

በተለይም በሐረርና በምሥራቅ የኢትዮጵያ ክፍሎች ያሉ የእስልምና ቅርሶች ከመውሊድ ትውፊት ጋር የተገናኙ ጥንታዊ የጽሑፍና የሥነ-ሥርዓት ሀብቶችን የያዙ ሲሆኑ፣ የበዓሉ አከባበርም የሀገራችንን ረጅም የጋራ የመኖርና የብዝኃነት ባህል አጉልቶ ያሳያል።

በዓሉ ማኅበራዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ በርካታ ሰብአዊ ተግባራት የሚከናወኑበት በመሆኑ፣ አቅመ ደካሞችን ማገዝ፣ የየቲሞችንና ምስኪኖችን ቀልብ መደሰት፣ ዘመድ አዝማድን መጠየቅ፣ እንግዶችን ማስተናገድና መልካም ምኞትን መለዋወጥ የበዓሉ ውብ ገጽታዎች ናቸው።

የዘንድሮው 1 ሺህ 501ኛው የነቢዩ ሙሐመድ (..) የመውሊድ በዓል እንደ ወትሮው ሁሉ የእስልምና እምነት ተከታዮችንና የመላው ሕዝቦቻችንን አንድነት በሚያጠናክር፣ ፍቅርና መፈቃቀር በሚጎለብትበት እንዲሁም በመረዳዳትና በመተሳሰብ መንፈስ የሚከበር ይሁን።

መልካም 1501ኛው የመውሊድ በዓል!

በብሌን ደምበሎ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: