በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በሚገኘውና የተፈጥሮ ሀብት በታደለው የኮንታ ዞን፣ አዲሱ ዓመት በልዩ ድምቀት ከሚከበርባቸው ታላላቅ ባህላዊ እሴቶች መካከል የ‘ህንግጫ’ በዓል ግንባር ቀደሙ ነው። ህንግጫ ቂም በቀል የሚረሳበት፣ ጠብ በእርቅ የሚዘጋበት እና ወጣቶች ሙሉ ነፃነታቸውን የሚያውጁበት ልዩ አጋጣሚ ነው።
በአስደናቂ ተፈጥሮዋና እና በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት በተገነባው ‘የዝሆን ዳና ሎጅ’ እንዲሁም በሌሎች የቱሪስት መስህቦች የምትታወቀው ኮንታ የህንግጫ በዓሏ ተጨማሪ የቱሪዝም መሰህብ ነው። ህንግጫ ከአሮጌው ዓመት ማብቂያ ጳጉሜ መጨረሻ አንስቶ እስከ መስከረም 16 ቀን ድረስ በተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች ይከበራል።
በዓሉ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከሚከበሩት እንደ አሸንዳ፣ አሸንዲዬ፣ ሻደይ እና ሶለል ካሉ የሴቶች በዓላት ጋር ተመሳሳይነት አለው። የኮንታ ልጃገረዶች ልዩ የነፃነት፣ የፍቅር፣ የሰላምና የደስታ መግለጫቸው የሆነውን ይህን በዓል በጉጉት ይጠብቁታል። በዚህ ወቅት ወጣቶች ተስፋን ያነገቡና አዲሱን ዓመት በደስታ መቀበል እንደሚገባ የሚያውጁ ዜማዎችን ያቀነቅናሉ።
አጋጣሚው ለወጣት ወንዶችና ሴቶች ለመተጫጨትና የህይወት አጋራቸውን ለመምረጥም ሰፊ ዕድል ይከፍታል። ከሙዚቃው፣ ከምግቡና ከባህላዊ ክዋኔዎቹ ባሻገር፣ በህንግጫ ወቅት ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው የእርቅ ሥነ-ሥርዓት ይከናወናል።
በዓሉ ከመድረሱ በፊት በባልና ሚስት፣ በቤተሰብ ወይም በጎረቤቶች መካከል የተፈጠረ ማንኛውም ቂም በእርቅ ይፈታል። ለዚህም ከ‘ማላ’፣ ‘አማራ’ እና ‘ዶገላ’ ከተሰኙት ሦስት ጎሣዎች የተወጣጡ ታላላቅ የሀገር ሽማግሌዎች ይሰየማሉ።
በእርቅ ሥነ ሥርዓቱ ላይ "አዋ" የሚባል የኮባ ቅጠል እና "ሰርዶ" ከውሃ ጋር ተቀላቅሎ እርግማንና ክፉ መንፈስ እንዲወገድ ይደረጋል። ሽማግሌዎቹም “የሚያጣላችሁ ሰይጣን ወደ ግራ ይሂድ፤ ሰላም ወደ ቀኝ ይምጣ” በማለት ሰላም ያወርዳሉ።
በበዓሉ ሰሞን እናቶች እና ልጃገረዶች እንሶስላ በመሞቅና አዳዲስ የባህል ልብሶችን በመልበስ ያሸበርቃሉ። ኮረዳዎች ለእነሱ ልዩ የነፃነት ቀናቸው በመሆኑ በሕብረት በመሰባሰብ "ሆሆሆያሆ ሰሎ..." የሚለውን ባህላዊ ዜማ እያዜሙ መንደሩን ያደምቁታል። በዚህ ጊዜ ማንም ሰው ሊከለክላቸውም ሆነ በነፃነታቸው ጣልቃ ሊገባ አይችልም።
ሴቶች ቤተሰቦቻቸውን በተለያየ የምግብና የመጠጥ ዝግጅት ሲያግዙ፣ ወጣት ወንዶች ደግሞ አካባቢውንና መንገዶችን በመመንጠር ሰፈሩን ያሰማምራሉ። ህንግጫ ከዘመን መለወጫ በዓልነቱ ባሻገር፣ የኮንታ ሕዝብ ማኅበራዊ አንድነቱን የሚያጠናክርበት ታላቅ የትውፊት ሀብት ነው።
በሲሳይ ደበበ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: