የኢፌዴሪ አየር ኃይል በቅርብ ዓመታት ያካሄደው ሁለንተናዊ የለውጥ ጉዞ የመደመር መንግሥት የተቋማት ግንባታና የሪፎርም አቅጣጫ በተግባር ፍሬ ማፍራቱን በግልጽ ያሳየ ነው።
ተቋሙን ከቀደመው የጥገና እና የዕድሳት ልምድ አውጥቶ ወደ ዘመናዊ፣ አስተማማኝ እና ስትራቴጂካዊ ብቃት ወዳለው ደረጃ አሸጋግሮታል።
ይህ ትራንስፎርሜሽን በቴክኖሎጂ፣ በዘመናዊ አሠራር፣ በሰው ኃይል ልማት እና በተቋማዊ አደረጃጀት ዙሪያ የተመዘገቡ አበይት እመርታዎችን ያካተተ ነው።
በዘመኑ የመከላከያ ቴክኖሎጂዎች ላይ በተደረገው ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የሀገራችንን አየር ክልል ሉዓላዊነት የመጠበቅ አቅም በአዲስ መልክ የተገነባ ሲሆን፣ ዘመናዊ የውጊያ እና የስለላ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በጥቅም ላይ በማዋል ስትራቴጂካዊ የክትትል እና የትክክለኛ ምት አቅም እንዲያድግ ተደርጓል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያን የአየር ክልል 24/7 በዘመናዊ ራዳሮች እና የቅድመ-ማስጠንቀቂያ ቴክኖሎጂዎች የማጠር አቅም በመገንባቱ አስተማማኝ ሀገራዊ ጥቃቅንና ማክሮ ደኅንነት ተረጋግጧል።
በዘመናዊ አሠራር እና በጥገና ራስን የመቻል እመርታ ያስመዘገበው ተቋሙ፣ ቀደም ሲል በውጭ ሀገራት ጥገኝነት ላይ የተመሰረተውን የአቪዬሽን ጥገና ወደ ሀገር ውስጥ በመቀየር በሀገር በቀል መሃንዲሶች አውሮፕላኖችን እና ሄሊኮፕተሮችን የማደስ፣ የውጊያ አቅማቸውን የመጨመር እና ደረጃቸውን የማሳደግ ሥራዎችን በተሳካ ሁኔታ በማከናወን ላይ ይገኛል።
በማንኛውም ዘመናዊ አደረጃጀት ውስጥ የቴክኖሎጂው ውጤታማነት በሰለጠነ የሰው ኃይል እንደሚረጋገጥ በመረዳት፣ በአቪዬሽን አካዳሚው ላይ ሰፊ ማሻሻያዎችን በማድረግ በዘመናዊ ሲሙሌተሮች እንዲደራጅ ተደርጓል።
በዚህም ወጣት መሃንዲሶች እና ፓይለቶች በዘመናዊ የጦር አቪዬሽን እውቀት እንዲታጠቁና የዕውቀት ሽግግር እንዲፋጠን በመደረጉ የተቋሙ የሰው ኃይል ግንባታ ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ አድጓል።
ፈጣን እና ትክክለኛ ውሳኔዎችን ለመስጠት የሚያስችል ዘመናዊ የዕዝ፣ ቁጥጥር እና የዲጂታል የመረጃ ልውውጥ ሥርዓት ከመዘርጋቱ ባሻገር፣ ለአባላቱ ምቹ የመኖሪያ፣ የህክምና እና የስፖርት ማዕከላት እንዲገነቡ መደረጉ የተቋሙን ዝግጁነትና የሰራተኞችን ተነሳሽነት በከፍተኛ ደረጃ ጨምሮታል።
የኢፌዴሪ አየር ኃይል ያስመዘገበው ይህ አጠቃላይ እመርታ፣ የመደመር መንግሥት የጀመረው የተቋማት ማሻሻያና የመልካም አስተዳደር ሪፎርም በተግባር ፍሬ ማፍራቱን የሚያረጋግጥ ከመሆኑም በላይ፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጠንካራ፣ ዘመናዊና መሪ የሆነ የአየር ኃይል የመገንባት ስትራቴጂካዊ እይታዋ ስኬታማ እየሆነ መምጣቱን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ሀገራዊ ኩራት ነው።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: