በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የሀገራችንን የረጅም ጊዜ የኅልውና፣ የልማት እና የፍትሃዊነት ፍላጎት ያማከለ የብሔራዊ ጥቅም ማረጋገጫ ነው።
የባሕር በር ባለቤትነት በቀጣናዊ ፖለቲካ፣ በዓለም አቀፍ ግንኙነት እና በኢኮኖሚ እድገት ውስጥ በቀላሉ የሚታይ ሳይሆን የሀገር ደኅንነት፣ የዲፕሎማሲ የመደራደር አቅም እና የብሔራዊ ኅልውና ዋና መለኪያ ነው።
ኢትዮጵያ ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ወደብ አልባ ሀገር መሆኗ እንዲሁም ሙሉ በሙሉ በሌሎች ሀገራት ወደቦች ላይ ጥገኛ መሆኗ የረጅም ጊዜ እድገቷን የሚገድብና ከፍተኛ የኢኮኖሚና የደኅንነት ዋጋ የሚያስከፍል ሆኖ ዘልቋል።
በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በመንግሥትና በሕዝብ እየተነሳ ያለው የባሕር በር ጥያቄ የሌሎችን ሉዓላዊነት ወይም ብሔራዊ ክብር ለመንካት የሚደረግ ሳይሆን፣ ከዓለም አቀፍ ህጎችና ታሪካዊ እውነታዎች ጋር የተያያዘ የህጋዊነትና የሰላማዊ ዲፕሎማሲ ጥሪ ነው።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት የጎረቤቶቿን ጥቅም የማይጋፋና በቀጣናው ላይ የጋራ ብልፅግናን እና ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት የሚያስችል የትብብር ጥያቄ ነው።
የዓለም አቀፍ ንግድ እንቅስቃሴ 80 በመቶ እንዲሁም የነዳጅና ኢነርጂ ዝውውር ከ70 በመቶ በላይ በባሕርና በውቅያኖሶች በኩል የሚከናወን በመሆኑ፣ ፍትሃዊ የባሕር በር አጠቃቀምን ማረጋገጥ ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ ትስስር ወሳኝ መሰረት ነው።
ሀገራት ወደቦችን ማዕከል ያደረጉ የነፃ ንግድ ቀጣናዎችን፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን፣ የሎጂስቲክስ ማዕከላትን እንዲሁም የባቡር፣ የመንገድ፣ የኃይልና የዲጂታል ኔትወርክ ግንባታዎችን በጋራ ሲያከናውኑ የሸቀጦች ዝውውር ይፋጠናል፤ የትራንስፖርት ወጪ በመቀነሱም ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ይሆናሉ።
በተጨማሪም አሠራርን ማዘመን፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የዕውቀት ልውውጥን በማስፋፋት ቀጣናውን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የኢኮኖሚ ማዕከል ለማድረግ ያስችላል።
በሌላ በኩል የባሕር በር ማግኘት በቀጣናው የደኅንነትና የኃይል ሚዛን ላይ ትልቅ ስፍራን ያጎናፅፋል። ታሪክ እንደሚያስረዳው ሀገራት ታላቅነታቸውን የገነቡት የባሕር በሮቻቸውን በመጠቀም፣ የባሕር ኃይላቸውን በማጠናከርና የንግድ መስመሮችን በመቆጣጠር ነው።
እንደ ባብ ኤል መንደብ ያሉ ወሳኝ የባሕር ሰርጦችን በጋራና በፍትሃዊነት መጠቀም ሀገራት የቀጣናውን ደኅንነት ከህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ከባሕር ላይ ውንብድና እና ከሽብርተኝነት በጋራ እንዲጠበቁ ያደርጋቸዋል።
ከዚህም ባሻገር በባሕር ስር የሚገኙ የማዕድን፣ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሀብቶችን ለመጠቀም፣ እንዲሁም የዓለምን 95 በመቶ የበይነ መረብ መረጃ የሚያጓጉዙ የፋይበር ኦፕቲክ ገመዶች ማለፊያ በመሆን የመረጃ ፍሰትን የመቆጣጠር አቅምን ይፈጥራል።
ኢትዮጵያ በጋራ ተጠቃሚነትና አብሮ በመበልፀግ መርህ ላይ ተመስርታ የምታቀርበው የባሕር በር ጥያቄ የራሷን የኢኮኖሚ ነፃነት የሚያረጋግጥ ከመሆኑም በላይ፣ በቀይ ባሕርና በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሁለንተናዊ እድገት፣ ዘላቂ ሰላምና የፖለቲካ ተፅዕኖ ላይ አዎንታዊ ማዕበል የሚፈጥር ስትራቴጂያዊ እርምጃ ነው።
በብሌን ደምበሎ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: