Search

ከሕዳሴው ግድብ ማማ እስከ ቀይ ባህር ዳርቻ የኢትዮጵያ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እና የቀጣናው ስትራቴጂካዊ ፖለቲካ

ቅዳሜ ነሐሴ 23, 2018 113

ኢትዮጵያ ታላቁን የሕዳሴ ግድብ በስኬት በማጠናቀቅ በመላው አፍሪካ አህጉር "ከእንግዲህ ይቻላል" የሚል አዲስ የተስፋና የሞራል ስንቅ መዝራቷን የፖለቲካ ተንታኙ ሙሳ ሸኮ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የታሪክ ጉዞም "ከሕዳሴ ግድብ በፊት እና በኋላ" በሚል አዲስ ስትራቴጂካዊ ምዕራፍ ውስጥ መግባቱን አስታውቀዋል።

የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያንም ትልቅ የሥነ-ልቦና እመርታን ያበሰረ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካ አንጋፋ ሀገር እንደመሆኗ መጠን አፍሪካውያን በራሳቸው እውቀትና ጉልበት እንዲህ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶችን እውን ማድረግ እንደሚችሉ በተግባር ያሳየችበት የታሪክ ማኅተም ነው።

ይህ ታላቅ ስኬት ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባህር ለመመለስና ፍትሐዊ የባህር በር ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ ለምታደርገው ጥረት ትልቅ ስትራቴጂካዊ ጉልበት የሚሆናት ነው።

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የቀይ ባህር ጥያቄ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አጀንዳ መሆን መቻሉንና የምዕራባውያን ሀገራትም የጥያቄውን ተገቢነት እየተረዱ መምጣታቸውን ተንታኙ ያመለክታሉ።

የፖለቲካ ተንታኙ የግብፅን ቀጠናዊ ሚና ሲተነትኑ፣ የካይሮ ስትራቴጂካዊ ትኩረት በኢትዮጵያ ላይ ብቻ ሳይሆን መላውን የአፍሪካ ቀንድ ማዳከም ላይ ያተኮረ መሆኑን አስረድተዋል።

ግብፅ ኤርትራን ከአፍሪካ ነጥላ እንድትቆይ ማድረጓ፣ በሱዳን አሁን ላለው ቀውስ ሰበብ መሆኗ እና በሌሎች የጎረቤት ሀገራት የምታደርገው ጣልቃ ገብነት የቀንዱን ቀጠና የመቆጣጠር እኩይ ፍላጎቷ አካል እንደሆነ ጠቁመዋል።

በተለይም ግብፅ ግዙፍ በጀት መድባ በአረብ ሚዲያዎች የምታደርገውን የሐሰት ፕሮፓጋንዳና የተዛባ ትርክት ለመመከት ኢትዮጵያ እውነታውን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚያደርስ ጠንካራና ተጽዕኖ ፈጣሪ የሚዲያ ቁመና ሊኖራት እንደሚገባም አሳስበዋል።

ግብፅ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማደናቀፍ የምታደርገውን እኩይ ሴራ ካላቆመች፣ ኢትዮጵያ በእጇ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት የመጠቀም ሕጋዊና ተፈጥሯዊ መብቷን እንደ ዲፕሎማሲያዊ መደራደሪያ ልትጠቀምበት እንደምትችል ሙሳ ሸኮ ጠቁመዋል።

ግብጾች የኢትዮጵያን የቀይ ባህር ተጠቃሚነት የሚቃወሙና አጥፊ ሴራቸውን የሚቀጥሉ ከሆነ፣ ኢትዮጵያም የራሷን የተፈጥሮ የውኃ ሀብት ወደ ሀገር ውስጥ አዙራ ለልማቷ የመጠቀም ተፈጥሯዊ መብት እንዳላትና ይህም ሀሳብ ያለ ምንም ፍርሃት በዲፕሎማሲያዊ መድረኮች ላይ በግልጽ ሊነሳ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በጥቅሉ፣ የሕዳሴው ግድብ ስኬት የኢትዮጵያን ቀጠናዊ የበላይነትና የልማት አቅም ያረጋገጠ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ በቀይ ባህርና በአፍሪካ ቀንድ የምትጫወተው መሪ ሚና ወደ አዲስ የታሪክ ማዕረግ የተሸጋገረበት ሁነኛ ማሳያ ነው።

 

በላሉ ኢታላ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: