ኢትዮጵያ የዜጎቿን ደኅንነት፣ ሉዓላዊነቷንና ሁለንተናዊ ዕድገቷን በማረጋገጥ በጽኑ መሠረት ላይ የተገነባ ተቋማዊ አቅሟን እና ሀገራዊ አንድነቷን በተግባር እያስመሰከረች ትገኛለች።
የፌዴራል መንግሥት ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ማግስት ጀምሮ በወሰዳቸው አዎንታዊ እርምጃዎች በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አቋቁሞ፣ ሕዝቡ ወደ ዕለታዊ የሥራ እንቅስቃሴው ተመልሶ የሰላምና የልማት ተጠቃሚ እንዲሆን ሰፊ ዕድል ማመቻቸቱ ይታወቃል።
ሆኖም ግን ይህንን የሰላምና የልማት አየር በመቃወም፣ ራሱን እንደ ሕጋዊ መንግሥት የሚቆጥረው ኋላቀሩ እና ሕገ-ወጡ የህወሓት ቡድን የትግራይን ሕዝብ ሰቆቃ ለማራዘም እያደረገ ያለው እኩይ እንቅስቃሴ የሀገራችንን ታላቅ የትራንስፎርሜሽን ጉዞ በፍጹም ሊያስተጓጉለው አይችልም።
ቡድኑ ሕጋዊውን ጊዜያዊ አስተዳደር በሴራ በማፍረስ፣ ከውጭና ከውስጥ አጥፊ ኃይሎች ጋር "ጽምዶ" የሚል ጥምረት በመፍጠር እና የኤርትራን መንግሥት መመሪያ በመቀበል ወጣቶችን እያፈሰ ወደ ወታደራዊ ካምፕ መውሰዱ የቀደመ የጥፋት ታሪኩ ማሳያ ነው።
የበርካታ ወጣቶችን ተስፋ ያጨለመውና ቤተሰቦችን የበተነው የዚሁ ቡድን አፈና ያስከፋቸው በርካታ የትግራይ ወጣቶች፣ ሕይወታቸውን ለማዳንና የተሻለ የሥራና የትምህርት ዕድል ፍለጋ ወደ አዲስ አበባና ሌሎች የሀገራችን ክልሎች በመፍሰስ ላይ ይገኛሉ።
የትግራይ ሕዝብ ከዚህ ጨካኝና ሕገ-ወጥ ቡድን መዳኛ መንገድ እየፈለገ በሚገኝበት በዚህ ወቅት፣ የፌዴራል መንግሥት የክልሉን ሕዝብ አጠቃላይ ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ዘላቂ ጥረት አጠናክሮ ቀጥሏል።
የትግራይም ሆነ የመላው ኢትዮጵያ ሕዝቦች የጋራ ፍላጎት ልማት፣ ሰላምና አብሮነት በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የትኛውንም አደናቃፊ ሴራ በመመከት የሀገራችንን የልማትና የስኬት ግብ እውን ማድረጉን በጽናት ይገፋበታል።
በጎሳዬ ገ/ኪዳን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: