Search

የኢትዮጵያና ታይላንድ ታሪካዊ ወዳጅነት ወደ ላቀ የኢኮኖሚና የንግድ አጋርነት እየተሸጋገረ ነው

ቅዳሜ ነሐሴ 23, 2018 86

ኢትዮጵያ ከታይላንድ ጋር ያላትን ዘመናት ያስቆጠረ ወዳጅነት ወደ ላቀ የኢኮኖሚ፣ የንግድና የኢንቨስትመንት አጋርነት ለመቀየር ቁርጠኛ መሆኗን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅ፣ እስያና ፓስፊክ ሀገራት ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ደዋኖ ከድር ገለጹ።

"ታይላንድ-ኢትዮጵያ የቢዝነስ ግንኙነትን መገንባት" በሚል መሪ ቃል የሁለቱ ሀገራት የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና የንግድ ማህበረሰብ አባላት የተሳተፉበት የሁለትዮሽ የቢዝነስ ፎረም በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በመድረኩ አምባሳደር ደዋኖ ከድር እንደተናገሩት፤ የሁለቱ ሀገራት ረጅም ዘመን ያስቆጠረ መልካም የፖለቲካ ግንኙነት ወደ ተጨባጭ የንግድና የኢኮኖሚ ትስስር ሊሸጋገር ይገባል።

በተለይም ታይላንድ በቱሪዝም፣ በግብርና ማቀነባበሪያ፣ በፋርማሲዩቲካልስ እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች ያላትን የበለጸገ ልምድና እውቀት ወደ ኢትዮጵያ ማምጣት የሚቻልበት ሰፊ እድል እንዳለ ጠቁመዋል።

አምባሳደሩ አክለውም ታይላንድ አዲስ ይፋ ያደረገችውን "የአፍሪካ-ታይላንድ ኢኒሼቲቭ" በማድነቅ፤ ጥረቱን ወደ ተጨባጭ የድርጊት መርሃ ግብር በመቀየር ግንኙነቱን የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ በግብርና፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም፣ በኢንዱስትሪ እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች ሰፊ የኢንቨስትመንት እድሎች ያሏት ሀገር መሆኗን በመጥቀስ፣ መጥተው ኢንቨስት ለማድረግ ለሚፈልጉ የታይላንድ ኩባንያዎችና ባለሀብቶች አስፈላጊው ሁሉ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ የታይላንድ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ጂሩሳያ ቢራናንዳ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ የምትገኝ ቁልፍ የኢኮኖሚ ማዕከል፣ ሰፊና እያደገ የመጣ ገበያ፣ ስትራቴጂካዊ መገኛ፣ የበለጸገ የግብርና ሀብትና እየተስፋፋ ያለ መሰረተ ልማት ያላት ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።

 

ይህ ሁኔታ ለዓለም አቀፍ ባለሀብቶች ሰፊ እድል የሚከፍት መሆኑን ጠቁመው፣ ታይላንድ ከኢትዮጵያ ጋር የምታደርገው አጋርነት የሥራ እድል የሚፈጥር፣ የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር የሚያመጣ እንዲሁም ለጋራ ብልጽግና አስተዋፅኦ የሚያደርግ እንዲሆን ፍላጎት እንዳላት አብራርተዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: