በአንድ ዓመት ብቻ 383 ሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች መገደላቸው ለንፁሃን ጥበቃ ማድረግ እንደሚገባ የማንቂያ ደወል ነው ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊነት ተቋም ኃላፊ ቶም ፍሌቸር አሳሰቡ።
በዛሬው ዕለት እየተከበረ ያለውን የዓለም የሰብዓዊነት ቀን ምክንያት በማድረግ ኃላፊው ባስተላለፉት መልዕክት፥ እ.አ.አ. በ2024 ግጭት ውስጥ በሚገኙ ሀገራት ሰብዓዊ ድጋፍ ሲሰጡ የነበሩ 383 ሠራተኞች ተገድለዋል ብለዋል።
በግጭት ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ድጋፍ ሲሰጡ በነበሩ ሰዎች ላይ ግድያ መፈፀሙ እንዲሁም ድርጊቱን የፈፀሙ አካላት በሕግ ተጠያቂ አለመሆናቸው ዓለም አቀፍ ሕግን የጣሰ አሳፋሪ ተግባር ነው በማለት አውግዘዋል።
የሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች በዓለም የሰዎች የጋራ እሴት ነፀብራቅ መሆናቸውን የተናገሩት የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማሀሙድ አሊ ዩሱፍ በበኩላቸው፥ ዓለም አቀፍ መርሆዎችን በተከተለ መንገድ ለመሥራት የፖለቲካ ቁርጠኝነት አስፈላጊ ስለመሆኑ አንስተዋል።
ግጭትን ተከላክሎ ሰላም በመፍጠር ዘላቂነት ያለው ኢንቨስትመንት እውን ማድረግ ይቻል ዘንድ በዓለም አቀፍ ደረጃ የባለብዙ ወገን አጋርነትና ትብብር እንዲጠናከር ጥሪ አቅርበዋል።
የአፍሪካ ሕብረት የሰብዓዊነት ተግባር ከሚሰሩ ተዋናዮች ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ለመሥራት ሁሌም ዝግጁ መሆኑንም ባወጣው መግለጫ አረጋግጧል።
በላሉ ኢታላ
#EBCdotstream #UNOCHA #WorldHumanitarianDay #aidworkerdeaths