Search

የኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ፕሮግራም እንዲሳካ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ ነን - ራፋኤል ማርያኖ ግሮሲ

ማክሰኞ ኅዳር 30, 2018 151

የኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ፕሮግራም እንዲሳካ ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ማርያኖ ግሮሲ ገለፁ፡፡ 

የዓለምአቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ማሪያኖ ግሮሲ ኢትዮጵያ የኒውክሌር መርኃ ግብር መጀመሯን አስመልክቶ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልእክታቸውም፤ በኢትዮጵያ ኒውክሌር ኮሚሽን መመስረት ባለራዕዩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የኢትዮጵያን መንግሥት እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እፈልጋለሁ ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ላቋቋመችውና ለሰላማዊ አገልግሎት ለሚውለው የኒውክሌር ኃይል ፕሮግራም ዓላማ መሳካት አለም አቀፍ የአቶሚክ ኤጀንስ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የኒውክለር ኃይል ኮሚሽን በማቋቋም ዘርፉ በህግ ስርዓት እንዲመራ በማድረግ ለሰላማዊ አገልግሎት የሚውል የኒውክሌር ኃይል ተግባራዊ እንዲሆን ለማድረግ ያከናወነቸውን ተግባር ዋና ዳይሬክተሩ አድንቀዋል፡፡ 

የተቋሙ መመስረት ዓለም አቀፍ ህግችን በተከተለ መንገድ ህጎችን በማውጣት ደህንነቱ አስተማማኝ የሆነ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫን እውን ለማድረግ እንደሚያስችልም ገልፀዋል፡፡ 

የኒውክሌር ኃይል ዝቅተኛ የበካይ ጋዝ ልቀት መጠኑ ያለው አስተማማኝ የኃይል ምንጭ በመሆኑ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማሳለጥ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

ለእቅዱ ውጤታማነት ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት ማስራት መጀመራታቸውን የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ተቋማቸው ለኢትዮያጵያ የኒውክሌር ኃይል ልማት ዓላማ ስኬት ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል፡፡

በላሉ ኢታላ

#Ebc #Ebcdotstream #Ethiopia #NuclearEnergy