በዲላ ከተማ የተሠራው የኮሪደር ልማት የነዋሪዎችን ማህበራዊ መስተጋብር ለማጠናከር ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።
የኮሪደር ልማቱ ከመሠራቱ አስቀድሞ የነበሩ መንገዶች ጠባብ ከመሆናቸውም ባሻገር ለትራፊክ አደጋ የሚያጋልጡ እንደነበሩ ነዋሪዎቹ ጠቅሰዋል።
በቅርቡ በከተማዋ የተከናወነው የኮሪደር ልማት ግን የከተማዋን ገጽታ ከመቀየሩ ባሻገር የትራፊክ ፍሰቱን ማሳለጥና ማህበራዊ መስተጋብሩንም ማጠናከር መቻሉን ነው የሚናገሩት።

የዲላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ መስፍን ደምሴ (ዶ/ር)፥ የከተማዋ ኮሪደር ልማት በሁለት ምዕራፍ እንደሚሠራ ጠቅሰው፤ በመጀመሪያው ምዕራፍ 10.5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የኮሪደር ልማት ሥራ መጠናቀቁን ገልጸዋል።
የኮሪደር ልማቱ የእግረኛ እና የብስክሌት መንገድ እንዲሁም የመዝናኛ ቦታዎችን ያካተተ መሆኑን አመላክተዋል።
በመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት በነበረው ንቁ የማህበረሰብ ተሳትፎ ለፕላን ማስጠበቅ ሥራ ከመንግሥት ካዝና ሊወጣ የነበረ 654 ሚሊዮን ብር ማዳን መቻሉ ተመልክቷል።
በምዕራፍ ሁለትም 10.5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የኮሪደር ልማት ሥራ እንደሚከናወን የተገለጸ ሲሆን፤ በዚህም የማህበረሰቡ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የተመራ የሚዲያ ባለሙያዎች ቡድን በዲላ ከተማ የተከናወኑ የልማታ ሥራዎችን ተዘዋውሮ ተመልክቷል።
በተመስገን ተስፋዬ
#EBCdotstream #Ethiopia #urbancorridor #Dilla