Search

ኢትዮጵያውያን መሥዋዕት የሆኑለትን የባሕር በር ስናገኝ ዕንባዬ ይታበሳል፦ የኮሞዶር ጌታቸው ስዩም ባለቤት

ሓሙስ ታኅሣሥ 09, 2018 87

ሀገራችን ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷ፣ ዕድገቷ እና ነፃነቷ እንዲጠበቅ በየዘመናቱ በርካታ የሕይወት እና የአካል መሥዋዕትነትን የከፈሉ ጀግኖች አያሌ ናቸው።

ከእነዚህ መካከል 1982 . ምፅዋ ላይ በነበረው ጦርነት ለጠላት እጅ አንሰጥም ብለው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ለብሰው መሥዋዕት የሆኑት ኮሞዶር ጌታቸው ስዩም አንዱ ናቸው።

በየካቲት 1982 . በምፅዋ እልህ አስጨራሽ ጦርነት ለሀገር ክብር እና ለባሕር በር ሲባል የባሕር ኃይል የሰሜን ዕዝ አዛዥ የነበሩት ኮሞዶር ጌታቸው ስዩም እና ኮሞዶር በለጠን ጨምሮ ሌሎች ሀገር ወዳዶች ለጠላት እጅ አንሰጥም በማለት ራሳቸውን መሥዋዕት ያደረጉ ጀግኖች መሆናቸውን ታሪክ ሲዘክረው ይኖራል።

ከኢቲቪ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኮሞዶር ጌታቸው ስዩም ባለቤት / ሣራ መኮንን፣ባለቤቴ የኢትዮጵያን የባሕር በር ለማስጠበቅ ሲባል ነው መሥዋዕት የሆኑትሲሉ ተናግረዋል።

ከሰላሳ ዓመታት በላይ ያለ አባት በብዙ ችግሮች ውስጥ ልጆቻቸውን ማሳደጋቸውን የሚገልጹት / ሣራ፣ ባለቤቴ ሕይወቱን የገበረለት ዓላማ ቢሳካ ያሳለፍኩት ችግር ሁሉ ይካሣል ይላሉ።

አሁን ላይ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከተዳፈነበት ወደ ሰላማዊ ጥያቄ በመምጣቱ እነኮሞዶር ጌታቸው ስዩም መሥዋዕት የሆኑለት ዓላማ እንዲሳካ መደረጉ ትልቅ ክብርም መሆኑን አውስተዋል።

የኢትዮጵያ ባሕር በር ተመልሶ ማየት ከቻልኩ በጣም ደስተኛ ከሚሆኑት ኢትዮጵያውያን መካከላንዷ እኔ ነኝ በማለት በዕንባ እና በቁጭት ተናግረዋል / ሣራ ጌታቸው።

የኢትዮጵያ መንግሥት የባሕር በር የማግኘት ጉዳይን ብሔራዊ ጥቅም አድርጎ መመልከቱ ለነገዋ ኢትዮጵያ የሚያስገኘው ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንደተጠበቀ ሆኖ ለባሕር በር ሲሉ ሕይወታቸውን ለገብሩ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የክብር ዋጋቸው የሚሆን ሥራ እንደሆነ ይሰማኛል ሲሉም ነው የገለጹት።

የኮሞዶር ጌታቸው ስዩም ልጆችም ምንም እንኳ የአባታቸው በሕይወት አለመኖር ጉዳቱ ብዙ እንዲሆን ቢያድርግባቸውም ስለአባታቸው ጀግንነት እና የሀገር ፍቅር ለመገንዘብ ችለዋል።

እናም ይህ የሀገር ፍቅር ስሜት ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ በመገንዘብ ለሀገራችን ያለንን ፍቅር ጽኑ እንዲሆን አድርጓል በማለት ይገልጻሉ።

በተለይ አሁን ጊዜው ደርሶ አባታችን መሥዋዕትነት የከፈለበት የባሕር በር ከመረሳት ወደ አጀንዳነት መምጣቱ በብዙ መንገድ ለእኛ የተለየ ነውሲሉ ነው የገለጹት።

በሜሮን ንብረት