Search

የኢትዮጵያ እና ህንድ ትብብር ለደቡብ ደቡብ አጋርነት ትልቅ አቅም ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ረቡዕ ታኅሣሥ 08, 2018 40

የኢትዮጵያ እና ህንድ የረጅም ጊዜ ስትራቴጂካዊ ትብብር ለደቡብ ደቡብ አጋርነት ትልቅ አቅም እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሕንዱ አቻቸው ናሬንድራ ሞዲ በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል በትናትናው ዕለት የክብር እራት ግብዣ አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ አሁን ላይ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈጠረው ስትራቴጂክ ግኑኝነት እያደገ በህዝባች መካከል የባህል ትስስር ፈጥሯል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያና በህንድ መካከል ለ1000 ዓመታት የዘለቀው ታሪካዊ ግኑኝነት በዲፕሎማሲ፣ በንግድ፣ በትምህርት እና በባህል ልቆ ወደ ስትራቴጂካዊ ትብብር መሻገሩንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በአፍሪካ አህጉር ላይ ያላቸውን ወጥ አቋም ያደነቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር)፤ ሌሎች ወዳጅ ሀገራትም በዚህ ላይ አጋርነታቸውን ማጠናከር አለባቸው ብለዋል፡፡

በጋራ ትብብር ላይ የተመሰረተው የኢትዮጵያ የእድገት አቅጣጫ  ከአፍሪካ የመነጨ፣ በአፍሪካዊ እሳቤ የሚመራና በአፍሪካ የሚተረጎም ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሉዓላዊነትን ያከበረ ዘመኑን የዋጀ አጋርነትና ተጨባጭ ትብብር ከህንድ ጋር ማድረግ ትፈልጋለች ብለዋል፡፡

የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በእኩልነት ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በደቡብ ዋልታ ጥምረት መርህ ላይ ያተኮረ መሆን እንዳለበትም ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጠንካራ እድገት እያሳያ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ባለፈው ዓመት 9.2 በመቶ እድገት ማሳየቱን ገልጸው፤ በዘንድሮ በጀት ዓመት ደግሞ 10.3 በመቶ እድገት ያስመዘግባል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ 650 የህንድ ኩባንያዎች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ተሰማርተው እንደሚገኙ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ይህን ወደ ጠንካራ ትብብር ማሳደግ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

በመሀመድ ፊጣሞ

#Ebc #ebcdotstream #AbiyAhmed #NarendraModi #Ethiopia #India