የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተጠናቀቀው 2018 በጀት ዓመት ከ8 ሺህ 985 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማቅረቡን አስታውቋል።
"የማዕድን ሀብታችን ለዘላቂ ብልፅግናችን" በሚል መሪ ሐሳብ የማዕድን ዘርፉን ምርታማነት ከማሳደግ ባለፈ፣ በዘርፉ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን ለመፍታት ያለመ ንቅናቄ መድረክ በአሶሳ ከተማ ተካሂዷል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በዘርፉ የሚታዩ ህገ-ወጥ ተግባራትን ለመከላከልና የሀገርን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል።
የማዕድን ዘርፉ የሀገር ኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፣ ዘርፉን በከፍተኛ ጥንቃቄና ትኩረት መምራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
በክልሉ የሚገኙ የወርቅ አምራች ፋብሪካዎች ዘርፉን ለማጠናከር ትልቅ አቅም እየሆኑ መምጣታቸውን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ እንደ ሀገርና እንደ ክልል የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል የንቅናቄው ፋይዳ የጎላ መሆኑን አብራርተዋል።
የክልሉ ማዕድን ቢሮ ኃላፊ አቶ ቲጃኒ አደም በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ 8 ሺህ 985 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ መላኩን ገልጸዋል። ቢሮው ከወርቅ ምርት በተጨማሪ የከሰል ድንጋይና የእምነበረድ ምርትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገርና የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን ለማሳደግ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለፉት 5 ዓመታት ከ1.18 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማስመዝቡንና ይህም ለሀገር ኢኮኖሚ እያበረከተ ያለውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያሳይ መሆኑን አንስተዋል።
ይሁን እንጂ በዘርፉ የሚስተዋሉ ህገ-ወጥ የማዕድን ግብይቶችና የአደገኛ ኬሚካሎች አጠቃቀም ክፍተቶች ተግዳሮቶች መሆናቸውን ገልጸው፣ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትና ከዘርፉ የሚገኘውን ሀገራዊ ጥቅም ለማሳደግ የተቀናጀ አሠራርና የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ አመላክተዋል።
በነስረዲን ሐሚድ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: