Search

የዳውሮ ብሔር የእርቅ፣ የይቅርታና የተስፋ በዓል - "ቶኪ ቤአ"

ሰኞ ነሐሴ 25, 2018 102
ክረምቱ ሲሸኝ፣ የከዋክብት እንቅስቃሴና የዕፅዋት ለውጥ ታይቶ አዲስ ዘመን ሲበሰር፤ ሰዎችን በአንድ ማዕድ የሚያስተናግድ ጥንታዊ የዘመን መለወጫ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ዳውሮ ብሔር በድምቀት ይከበራል።
ደማቅ ባህልና ጥንታዊ ታሪክ ባለቤት የሆነው የዳውሮ ብሔር፣ የራሱ የካቲ ንጉሠ ነገሥት ሥርዓትና ሀገር በቀል የዘመን አቆጣጠር ያለው ማህበረሰብ ነው። በዚህ ማህበረሰብ ዘንድ ከጥንት ጀምሮ የመጣው "ቶኪ ቤአ" የዘመን መለወጫ በዓል፣ ከአዲስ ዓመት መባቻነት ባለፈ ለሰላም፣ ለእርቅና ለተፈጥሮ ጥበቃ የሚሰጠው ቦታ ከፍተኛ ነው።
"ቶኪ ቤአ" በዳውሮኛ ቋንቋ የክረምቱን ጨለማና ዝናብ ሽኝቶ፣ የብርሃንና የምርት መሰብሰቢያውን አዲስ ዘመን መቀበልን ያመላክታል።
ይህ በዓል በግምት የሚወሰን ሳይሆን፣ የባህል አባቶች የከዋክብትን፣ የጨረቃንና የፀሐይን እንቅስቃሴ በማጥናት እንዲሁም የአየር ንብረትና የዕፅዋት ለውጥን በመመልከት ቀኑን የሚወስኑበት ጥንታዊ ሀገር በቀል የስነ-ከዋክብት ጥበብ መገለጫ ነው። የከረምት እርሻ ተጠናቆ መስከረም ሲጠባ፣ ማህበረሰቡ ለፈጣሪው ምስጋና ያቀርባል።
የቶኪ ቤአ ዋነኛ ውበቱ በማህበራዊ እሴቱ ላይ ነው። በበዓሉ ዋዜማ በሰዎች መካከል የነበረ ቂምና አለመግባባት በሀገር ሽማግሌዎች ይፈታል። የተጣሉ የሚታረቁበት፣ የተራራቁ የቤተሰብ አባላት በአንድ ማዕድ የሚሰበሰቡበት፣ ያለው ለሌለው የሚያካፍልበት የይቅርታና የተስፋ በዓል ነው።
ቶኪ ቤአን ልዩ የሚያደርገው ሌላው እሴት ደግሞ የተፈጥሮና የእንስሳት እንክብካቤ ባህሉ ነው። በበዓሉ ዕለት የቤት እንስሳት ጠግበው እንዲውሉ ልዩ መኖ ይቀርብላቸዋል።
በዓሉ በቡላ፣ ቆጮና ቅቤ በሚዘጋጁ ባህላዊ ምግቦች፣ በማራኪ የጥጥ አልባሳት፣ የእጅና የአንገት ጌጣጌጦች እንዲሁም በልዩ የቶኪ ቤአ ዜማዎች ይደመቃል። ይህ ኩነት የቱሪዝም እምቅ አቅሙ ከፍተኛ ከመሆኑ ባሻገር የአካባቢውን የንግድና የግብርና እንቅስቃሴ ያነቃቃል።
ቶኪ ቤአ የሰው፣ የተፈጥሮና የከዋክብት ድንቅ ቁርኝት! ጥንታዊውን የአባቶች እውቀት በጋራ የያዘ የኢትዮጵያ ዕሴት ነው፡፡
በሲሳይ ደበበ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: