አርበኝነት በኢትዮጵያውያን ደም ውስጥ የሰረጸ፣ በታሪካችን ማህደር በደማቁ የተጻፈ የኢትዮጵያውያን ዘመን ተሸጋሪ ህያው መለያ ነው።
ኢትዮጵያዊ ስለ ሀገሩ ፍቅር እስከ ጥግ የሚሄድ፣ ራሱን የሚሰዋ እና ከእናት ከአባቱ በክብር የወረሰውን የሀገር ፍቅር በምንም የማይለውጥ አርበኛ በመሆኑ፣ አርበኝነት ለኢትዮጵያውያን ከስሜት ያለፈ ተጨባጭ እሴት እንዲሁም የነፃነትና ሉዓላዊነት መገለጫ ምስክር ነው።
በታሪክ አጋጣሚዎች የተከሰቱትን የውጭ ወረራዎችን በመመከትና ሀገራዊ ነፃነትን በማስከበር መሠረት ላይ የታነፀው ይህ የትውልድ ታላቅ አቅም፣ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት፣ የኩራት እና የፀረ-ኮሎኒያሊዝም አህጉራዊ ተምሳሌት ሆኖ አገልግሏል።
በዚህኛው ትውልድ ደግሞ አርበኝነት ከጦር ሜዳ ውጊያ ባሻገር የሀገርን ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት እና የውኃ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የጠየቀ በመሆኑ፣ አዲሱ ትውልድ የህልውናው መሠረት የሆነውን የባሕር በር ጥያቄ በጽናት አንግቦ ተነስቷል።
ኢትዮጵያ ቀጥተኛ የባሕር በር ፍላጎቷን በግልጽ ማንሳቷ ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ጂኦ-ፖለቲካዊ መሠረት ያለው ሲሆን፣ የባሕር በር ጥያቄ ለኢትዮጵያውያን የንግድ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን የህልውና፣ የውኃ ሉዓላዊነት እና የዘላቂ ዕድገት ወሳኝ ጉዳይ ነው።
አባቶቻችን ዳር ድንበሯን በደም አስከብረው እንደጠበቁን ሁሉ፣ የዛሬው ትውልድ ደግሞ ሀገራችንን ከድህነት እና ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ለማውጣት የባሕር በር ማግኘትን እንደ ዘመናዊ የአርበኝነት ግዴታና ብሔራዊ ተልዕኮ ይቆጥረዋል።
የባሕር በር ጥያቄ ከኢትዮጵያ ፍላጎት ባሻገር ለመላው አፍሪካና ለምስራቅ አፍሪካ አህጉራዊ ዕቅዶች ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ካላት ግዙፍ የሕዝብ ቁጥር አንጻር ቀጥታ የባሕር በር ማገኘቷ የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጠና ግብ የሆነውን የአህጉር ውስጥ ንግድ ያፋጥነዋል።
በተጨማሪም ለወደብ አገልግሎት የምታወጣውን በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ወጪ ወደ ልማት ማዞር የሚያስችል እና ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራት አማራጭ የሎጂስቲክስ መስመሮችን በመክፈት የንግድ ወጪን የሚቀንስ ነው።
በሌላ በኩል የቀይ ባሕር እና ባብ ኤል መንደብ መስመር ለዓለም አቀፍ ንግድ ወሳኝ በመሆናቸው፣ ኢትዮጵያ በቦታው ቀጥተኛ ሚና ማግኘቷ የባሕር ላይ ወንበዴነትን፣ ሕገ-ወጥ ዝውውርን እና የባሕር ላይ ደኅንነትን ለማስጠበቅ የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ ያጠናክራል።
ኢትዮጵያውያን አባት አርበኞች በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች የገጠሟቸውን ወራሪዎች አሳፍረው በመመለስ ያስመዘገቡት ታሪካዊ ድል ከራስ አልፎ ለመላው አፍሪካ አርአያ እንደሆነ ሁሉ፣ የዘመኑ ወጣት አርበኛም የውኃ ሉዓላዊነቱን በመጠበቅና ለባሕር በር ጥያቄው ዘላቂ ምላሽ በመስጠት ለትውልድ የሚሻገር ታሪካዊ መልህቅ እና አዲስ አሻራ ያስቀምጣል።
በአይናለም ሀድራ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: