የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት በራስ ዐቅም ያከናወናቸው ተግባራት ኢትዮጵያ አሳታፊና አካታች ልማትን እያረጋገጠች ያለች ሀገር መሆኗን የሚያሳዩ መሆናቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለፁ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው፣ ዛሬ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት በራስ ዐቅም ያከናወነውን ውጤታማ ተቋማዊ ሪፎርም በአገልግሎቱ ዋና መሥሪያ ቤት ቅጥር ግቢ ተገኝተን ተመልክተናል ብለዋል።
ይህ ሪፎርም የሥራ ቦታን ከማሻሻል ባለፈ፣ የሥራ ባህልን፣ የአገልግሎት ጥራትንና ተቋማዊ ዐቅምን የሚያጎለብት ለውጥ መሆኑንም አብራርተዋል።
የአገልግሎቱ አመራሮች፣ ሠራተኞችና ስደተኞች በመቀናጀት በዋና መሥሪያ ቤቱ፣ በ8 ክልሎች በሚገኙ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችና በ25 መጠለያ ጣቢያዎች ያከናወኑት ሥራ፣ በራስ ዐቅም ተቋማዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ያሳየ ጥሩ ተሞክሮ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይም የመደመር መንግሥት የግብርና እመርታ ማሳያ የሆነውን የሌማት ትሩፋትን በመጠቀም በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በዶሮና እንስሳት እርባታ፣ በንብ ማነብና በተለያዩ የዕጽዋት ልማት ዘርፎች የተጀመሩ ሥራዎች፣ ተቋማዊ ሪፎርም የሚለካው በተሻለ የሥራ አካባቢ ብቻ ሳይሆን በሚፈጥረው ምርታማነትና ውጤት ጭምር መሆኑን የሚያሳዩ መሆናቸውን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ዓለም አቀፍ ስደተኞችን በመቀበል፣ መብትና ክብራቸውን በማስጠበቅ ከተቀባዩ ማኅበረሰብ ጋር በማስተሣሠር በልማት ዕድሎች ተጠቃሚ እያደረገች መሆኗን የተናገሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ስደተኞቹ የዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ መሆናቸውም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፏቸውን እያሳደገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በራስ ዐቅም የሚመጣ ለውጥ የተቋምን ዐቅም እንደሚያጎለብት እና ይህ ደግሞ የሀገርን ዐቅም እንደሚገነባ የገለፁት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፤ በስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት የታየው ስኬታማ ጉዞ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: