Search

ከግለሰቦች በላይ - የክብር ማኅተም የሆነው አትሌቲክሳችን እና የተፈተነው ንግሥናችን

ሰኞ ነሐሴ 25, 2018 126
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ከግለሰቦች ፍላጎት እና ከወቅታዊ የሥልጣን ውዝግብ በላይ የሆነ፣ የሀገር ፍቅር እና የማንነታችን መገለጫ የሆነ ታላቅ ሀገራዊ ሀብት ነው።
በዓለም አደባባይ የአረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ሰንደቃችን ከፍ ብሎ ሲውለበለብ፣ ከድል በላይ የሆነ ስሜት ይፈጠራል። የብዙ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን የደስታ፣ የጽናት እና የጋራ ኅብረት ምንጭ ሆኖ ኖሯል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ታሪክ በባዶ እግራቸው ዓለምን ካስደመሙት የጀግንነት ገድሎች ጀምሮ እስከ አሁኖቹ ወጣት ባለታሪኮች ድረስ በደም፣ በላብና በጥቁር ሕዝቦች የነጻነት አርማ ተምሳሌትነት የተገነባ የክብር ማኅተም ነው።
አትሌቶቻችን የሚሮጡት ለግል ዝና ብቻ ሳይሆን፣ የሕዝብን ተስፋ እና ሀገራዊ ክብር በልቦቻቸው ተሸክመው ነው።
ይህ ታላቅ የድል ታሪክ ሕዝቡን የዘር፣ የሃይማኖት እና የፖለቲካ ልዩነት ሳይገድበው መላውን ኢትዮጵያዊ በአንድ ልብ የሚያቆም የኅብረታችን ጠንካራ ምሶሶ ነው።
ሆኖም ስፖርቱ አሁን ካለበት የአመራር ውጥረት እና የውጤት ውጣ ውረድ ወጥቶ ዘላቂ ተቋም ይሆን ዘንድ የሁሉም አትሌቲክስ ወዳድ የበሰለ ውሳኔ እና ጥረት ያስፈልገዋል።
አትሌቲክሱ ከግለሰባዊ ሽኩቻ በላይ በመሆኑ ሕግን፣ ተቋማዊ አሠራርን እና የሙያ የበላይነትን ማስቀደም ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው።
የፌዴሬሽኑ አሠራር በግልጽነት፣ በተጠያቂነት እና በግልጽ የሥራ ድርሻ ክፍፍል ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት። ደንብ እና መመሪያ በማክበር፣ የሥራ ድርሻን በግልጽ በመለየት እና ውሳኔዎችን በሙያዊ መርሕ በመወሰን ተቋሙን ከግለሰባዊ ተጽዕኖ መጠበቅ ይገባል።
ውስጣዊ አለመግባባቶችን በሰከነ ውይይት በመፍታት የአትሌቶቻችንን ሥነ-ልቦና ከአደጋ መጠበቅ ይገባል።
የአትሌቲክሱ ዘላቂ ስኬት የሚለካው በዛሬ ሜዳሊያ ብቻ አይደለም። የነገ አትሌቶችን በማፍራት፣ የሥልጠና ማዕከላትን በማጠናከር፣ የአሠልጣኞችን እና የቴክኒክ ባለሙያዎችን አቅም በማሳደግ እንዲሁም ሳይንስ እና ቴክኖሎጂን ከስፖርቱ ጋር በማቀናጀት ነው።
ማንኛውም በስፖርቱ ላይ የሚደረግ ሪፎርም የግለሰቦችን የበላይነት ሳይሆን፣ የረጅም ጊዜ ሀገራዊ ጥቅም፣ የፋይናንስ አጠቃቀም፣ የአትሌቶች መረጣ፣ የዓለም አቀፍ ጉዞዎች እና የውድድር ዝግጅቶች በግልጽ መሥፈርት እና በሙያዊ ጥናት እንዲመሩ ሊያግዝ መሆን አለበት።
ይህ የሚጠቅመው ተቋሙን ብቻ ሳይሆን፣ የአትሌቶችን መብት፣ ዕድል እና የወደፊት ሕልም እንዲሁም ስፖርቱንም ነው።
በተለይ የወጣቶች ተሰጥኦ ልየታ እና ልማት ላይ የሚደረገው ሥራ የአትሌቲክሱ የነገ መሠረት ነው። የዛሬን ሻምፒዮኖች ለማክበር ብቻ ሳይሆን፣ የነገ ሻምፒዮኖችን ለማፍራት የሚችል ሥርዓት መገንባት ይገባል።
ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ያላትን የንግሥና ዙፋንን አጠናክራ እንድትቀጥል፤ የስፖርቱ አስተዳደር በይቅርታ፣ በአንድነት እና በበሰለ አመራር ሊመራ ይገባል። የዛሬ ውሳኔ የነገን አትሌቲክስ ስለሚወስን፣ የግል ሽኩቻን በማስቀረት የትውልድን አደራ ማስቀደም ግድ ይላል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ የትናንት ትውልድ በባዶ እግሩ የገነባው፣ የዛሬው ትውልድ የተረከበው እና የነገው ትውልድ የሚወርሰው ሀገራዊ አደራ ነው።
ስፖርቱን የሚመሩ ሰዎች ይቀየራሉ፤ አመራሮች ይመጣሉ፣ ይሄዳሉ፤ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ግን ከሁሉም በላይ ሆኖ መቀጠል አለበት።
የአትሌቲክሱ ጉዳይ የግለሰቦች ወይም የተቋም ብቻ ሳይሆን የሀገር ጉዳይ ነው። ምክንያቱም አትሌቲክሳችን ስፖርት ብቻ አይደለም፤ የኢትዮጵያ ክብር፣ የሕዝቧ አንድነት እና የትውልዶች ተስፋም ጭምር ነው።
በአዲስ የሺዋስ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: