Search

ከስድስት ሰከንድ በላይ የማይዘገዩት የጃፓን ባቡሮች

ረቡዕ ነሐሴ 14, 2017 102

የጃፓን የባቡር ትራንስፖርት ድርጅት በምድር ባቡር ትራንስፖርት ዘርፍ አስገራሚ ተሞክሮዎች አሉት።

ይህ ዘመናዊ ድርጅት እጅግ ፈጣን በሆኑ የኤሌትሪክ እና በሌሎች ሃይሎች የሚሰሩ ባቡሮችን ተጠቅሞ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

በቀንም 15.6 ሚሊየን ለሚደርሱ መንገደኞች የትራንስፖርት አገልግሎት ይሰጣል።

በጃፓን የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ሊዘገይ የሚችልባቸው አጋጣሚዎች እጅግ አነስተኛ ናቸው።

በተለይ እንደ ሺንካንሰን ቡሌት ያሉት እጅግ ፈጣንና ዘመናዊ ባቡሮች ሁሌም በሰዓት ተገኝተው ነው ተሳፋሪዎችን የሚያስተናግዱት።

እነዚህ በሰዓት 320 ኪሎ ሜትር የሚጓዙት ፈጣን ባቡሮች ምናልባት እክል ገጥሟቸው ዘገዩ ከተባለም ከስድስት ሰከንድ በላይ አይቆዩም።

ስድስት ሰከንዶች ሲዘገዩም የኩባንያው አስተዳደሮች ከወገባቸው ዝቅ ብለው ደንበኞቻቸውን ይቅርታየተጠቁበት ወቅትም አለ።

ይህም ጃፓኖች ለሰዓት ማክበር ያላቸውን ጠንካራ ባህል ያሳያል።

እ.አ.አ. በ1964 የተመሰረተው ይህ የሺንካሰን የምድር ባቡር ድርጅት ሌላው የሚታወቅበት አስደናቂ ነገር አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ጊዜ እስካሁን ድረስ በሰው ሕይወት ላይ ያስከተለው የሞት አደጋ አለመኖሩ ነው።

በባቡር ትራንስፖርት ዘርፍ ሌላው የሚጠቀሰው እ.አ.አ. በ1853 የተመሰረተው የሕንድ የባቡር ትራንስፖርት ድርጅት ነው።

ይህ ግዙፍ ድርጅት በዓለም ላይ በርካታ ሰዎችን መቅጠር ከቻሉ ድርጅቶች መሀከል በስምንተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

በሁለት ሺህ የህንድ ከተሞች የሚገኙ 7,172 የባቡር ጣቢያዎች ያሉት የህንድ የባቡር ድርጅት 14 ሺህ የሰው ማጓጓዣና ዘጠኝ ሺህ የእቃ በድምሩ 23 ሺህ የሚደርሱ ባቡሮች ያሉት ሲሆን በቀን 23 ሚሊየን መንገደኞችን እና ከ4 ሚሊዮን ቶን በላይ የሚሆን ጭነት ያጓጉዛል።

በሚያስተዳድራቸው ሰራተኞች ብዛት በሚያመላልሳቸው መንገደኞች እንዲሁም በመቶሺዎች በሚቆጠሩ ፉርጎዎች በግዙፍነቱ የሚታወቀው ይህ የህንድ የባቡር ድርጅት 327,991 የእቃ ማመላለሻ ፉርጎዎችም ባለቤት ነው።

በተጨማሪም ከ91 ሺህ በላይ ነው ለሰዎች የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡት ፉርጎዎችም አሉት።

የህንድ የምድር ባቡር ድርጅት ሌላው የሚታወቅበት ከኤዥያ ተወዳዳሪ በሌለው ረጅም የባቡር ሀዲድ መስመሩ ነው።

ይህ የባቡር ሀዲድ 68 ሺህ ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን በዓለም በርዝመቱ የአራተኛ ደረጃን ይዟል።

 

በዋሲሁን ተስፋዬ

#EBC #ebcdotstream #railways #technology