Search

ለአዲሱ ዓመት በዓል የፍጆታ ዕቃዎችን በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ ዝግጅት ተደርጓል - የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ

ማክሰኞ ነሐሴ 26, 2018 142

2019 አዲስ ዓመት በዓልን በማስመልከት በቂ የምርት አቅርቦት ማዘጋጀቱን እና የገበያ መረጋጋትን ለማረጋገጥ ያለመ የቁጥጥር ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ አስታውቋል።

የበዓሉን አከባበር የተሳካ እና ሰላማዊ ለማድረግ ከንግድ ማኅበረሰቡ ጋር ሰፊ ውይይቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን የቢሮው ኃላፊ / ሀቢባ ሲራጅ ገልጸዋል።

እንደ ኃላፊዋ ገለጻ፣ መንግሥት ከፍተኛ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ የምርት አቅርቦት እና ቁጥጥር ሥራዎችን በስፋት ሲያከናውን ቆይቷል።

በዚህም መሠረት በቂ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች የቀረቡባቸው 7 የግብይት ማዕከላት፣ 264 የሰንበት ገበያዎች፣ 5 የቁም እንስሳት የግብይት ማዕከላት፣ እንዲሁም በሁሉም 11ዱም ክፍለ ከተሞች የንግድና ኤግዚቢሽን ባዛሮች ተዘጋጅተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።

ከዚህ በተጨማሪም የአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ለበዓሉ የምግብ ዘይት እና የስንዴ ዱቄትን ጨምሮ አስፈላጊ የሚባሉትን ምርቶች በበቂ ሁኔታ ወደ ከተማዋ በማስገባት ሙሉ ዝግጅት ማጠናቀቃቸው ተገልጿል።

ለኅብረተሰቡ የተረጋጋ የገበያ ፍሰት ለመፍጠር የገበያ ትስስር ሥራዎች በስፋት መመቻቸታቸውን የጠቆሙት ወይዘሮ ሀቢባ፣ ህገወጥነትን ለመግታት የተቀናጀ የቁጥጥር ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

በተለይም በዓሉን ምክንያት በማድረግ የመጋዘን ፍተሻ ማካሄድ፣ የምርት ጥራትና የዋጋ ጭማሪ ቁጥጥር፣ የኮንትሮባንድ ንግድና የንግድ ሚዛኖች ትክክለኛነት (ግራም) ማረጋገጥ፣ ባዕድ ነገር የተቀላቀለባቸውን ምርቶች ማጋለጥ፣ እንዲሁም የደላሎችን ጣልቃ ገብነትና ህገወጥ ነጋዴዎችን የመቆጣጠር ሥራ በልዩ ሁኔታ ይከናወናል።

እነዚህን ተግባራት በብቃት ለማከናወን አስፈላጊው የቁጥጥር ግብረ-ኃይል ተሰማርቶ ወደ ሥራ የገባ ሲሆን፣ ቁጥጥሩ በዓሉ እስኪያልፍ ድረስ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል።

ኃላፊዋ አክለውም ህብረተሰቡ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪና ህገወጥ የግብይት እንቅስቃሴዎችን ሲመለከት ጥቆማ በመስጠት እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል።

በተጨማሪም የንግድ ማኅበረሰቡ አላስፈላጊ አሰራሮችን በማስወገድ የተጣለበትን ኃላፊነት እንዲወጣ፤ ሚዲያዎችና ባለድርሻ አካላትም ትክክለኛ መረጃ በመስጠትና በመቆጣጠር ረገድ ድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አስተላልፈዋል።

በሂሩት እምቢአለ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: