የኢትዮጵያን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን በማፋጠን ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተ የሚገኘው አንጋፋው ተቋም ኢትዮ ቴሌኮም፤ ከዋና ተልዕኮው ባሻገር ማኅበራዊ ፋይዳቸው የጎሉ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን በማከናወን መልካም አሻራውን ማሳረፉን ቀጥሏል።
ተቋሙ በዛሬው ዕለት ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ለተማሪዎች የሚውል ከ188 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የገንዘብ እና የትምህርት ቁሳቁስ፣ እንዲሁም ሀገራዊ የደም ልገሳ መርሐ ግብር አካሂዷል።
ተቋሙ “በበጎነት” በሚል ስያሜ በቀረጸው ልዩ መርሐ ግብር፣ በመላ ሀገራችን ለሚገኙ 50 የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ከ75 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።
በዚህም በእነዚህ ተቋማት ጥላ ሥር ለተጠለሉ 22 ሺህ 212 አረጋውያን፣ ሕፃናት፣ እናቶች፣ አካል ጉዳተኞች እና አቅመ ደካሞች የዕለት ተዕለት ሕይወት መሻሻል የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል።
ኢትዮ ቴሌኮም ይህንን ማኅበራዊ ግዴታውን ላለፉት አምስት ተከታታይ ዓመታት የፈጸመ ሲሆን፣ የዘንድሮውን ጨምሮ እስካሁንም ከ117 በላይ ለሚሆኑ የበጎ አድራጎት ተቋማት የድጋፍ እጁን ዘርግቷል።
ኩባንያው የነገ የሀገር ተረካቢ ትውልዶችን ለመደገፍ ትምህርትን መሠረት አድርጎ፣ “ለነገ ተስፋዎች” በተሰኘው መርሐ ግብሩ ሰፊ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
በዚህም በመላው ሀገራችን አነስተኛ ገቢ ካላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ለተውጣጡ 105 ሺህ 496 የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች፤ ከ113 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የመማሪያ ደብተሮችን አበርክቷል።
ኩባንያው የዘንድሮውን ጨምሮ ባለፉት ሰባት ተከታታይ ዓመታት በተተገበረው በዚህ መርሐ ግብር፤ ከ434 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ከ483 ሺሕ 800 በላይ ተማሪዎችን መደገፍ ችሏል።
ከገንዘብ እና ከቁሳቁስ ድጋፉ ጎን ለጎን፣ ተቋሙ “በጎነት ለሰብዓዊነት” በሚል መሪ ሐሳብ ከብሔራዊ የደም ባንክ ጋር በመተባበር ሕይወት አድን የደም ልገሳ መርሐ ግብር አካሂዷል።
ዋና መሥሪያ ቤቱን ጨምሮ በዞን እና በሪጅን ጽሕፈት ቤቶች በሚገኙ በአጠቃላይ 22 ማዕከላት፤ የኩባንያው የሥራ ኃላፊዎች እና በጎ ፈቃደኛ ሠራተኞች ደማቸውን በመለገስ ያላቸውን ወገናዊ አለኝታነት በተግባር አረጋግጠዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም እያከናወናቸው ያሉት እነዚህ የድጋፍ መርሐ ግብሮች፣ ኩባንያው ቴክኖሎጂን ከማቅረብ ባለፈ የዜጎችን ማኅበራዊ ሕይወት በማሻሻል በኩል እያሳረፈ ያለውን ጉልህ አዎንታዊ አሻራ የሚያሳዩ ናቸው።
በሳምሶን በላይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: