በተጠናቀቀው 2018 በጀት ዓመት 33.5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በሰብል በመሸፈን ከ1.85 ቢሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ መቻሉን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 የዕቅድ ትውውቅ መድረክ በቢሸፍቱ ከተማ ማካሄድ ጀምሯል።
በቀረበው ሪፖርትም በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የተገኘው ከ149 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት፣ ሀገራችን በውጭ ስንዴ ላይ የነበረባትን ጥገኝነት በማስቀረት ረገድ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑ ተመላክቷል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የተመዘገበው ውጤት ሀገራዊ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚከናወነው ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የሚያሳይ ነው።
ለምርታማነቱ ዕድገት ደግሞ የግብዓት አቅርቦት መሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸው፣ በዚህም በበጀት ዓመቱ ከ20 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች ማሰራጨት ተችሏል ብለዋል።
እንደ ሀገር በ"ሌማት ትሩፋት" መርሐ ግብር ከ15.8 ቢሊዮን ሊትር በላይ ወተት፣ 427.9 ሺህ ቶን ማር እንዲሁም 11.7 ቢሊዮን እንቁላል በማምረት የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትን የማሻሻል ሥራ መከናወኑ ተገልጿል።
በዓመቱ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርም 7.7 ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸውንና የሀገራችን የደን ሽፋን 23.6 በመቶ መድረሱን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ በውጭ ንግድ ዘርፍ ከቡና፣ ከአበባ፣ ከቅባት እህሎች እና ከእንስሳት ተዋፅኦ ከ4.55 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት መቻሉን አብራርተዋል።
በግብርናው ዘርፍ የተጀመሩ የሜካናይዜሽን ሥራዎች በ2019 በጀት ዓመትም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገልጿል።
በአለም ይልፉ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: