በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ኦሮሚያ ዞን አባያ ወረዳ ውስጥ የሚገኘው እና 149 ሄክታር መሬት የሚሸፍነው የዋለሜ ፍል ውኃ ድንቅ የተፈጥሮና የኢኮ-ቱሪዝም መዳረሻ ነው።
ከአዲስ አበባ በ377 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ይህ ስፍራ፣ በጓንጓ ከተማ በኩል ከዋናው የአስፓልት መንገድ ወደ ቀኝ በመታጠፍ የ5 ኪሎ ሜትር ጉዞ ሲደረግ ይደረስበታል።
የዋለሜ ፍል ውኃ ያለው ዘርፈ-ብዙ የጤና ፈዋሽነት ከአካባቢው ማራኪ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ጋር ተዳምሮ ልዩ ገጽታ አላብሶታል።
በአሁኑ ወቅት ስፍራው በወረዳው አስተባባሪነት እና በማኅበረሰቡ ተሳትፎ በተገነቡ ውስን መሠረተ ልማቶች አማካኝነት ለአካባቢው ነዋሪዎች የፍል ውኃ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
ይሁን እንጂ ፍል ውኃው ለምን ዓይነት አገልግሎቶች መዋል እንደሚችል በዝርዝር የሚለይ ሳይንሳዊ ጥናት ገና ያልተካሄደለት ሲሆን፣ በቂ የመሠረተ ልማት አለመሟላትም መዳረሻው ከያዘው ሰፊ እምቅ አቅም አንጻር ጎብኚዎችን በበቂ ሁኔታ እንዳይስብ አድርጎት ቆይቷል።
ሆኖም ስፍራው የፍል ውኃውን መነሻና አካባቢውን የሚያካትት ዘመናዊ የስፓ ሪዞርትና የመዝናኛ ማዕከል ለማልማት እጅግ ምቹ መሆኑን ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
ይህ የዋለሜ የተፈጥሮ ሀብት ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶት ቢለማ፣ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ብቻ ሳይሆን፣ ለኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት ትልቅ አቅም እንደሚሆን ይታመናል።
በብርቱካን አስናቀ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: