በየዓመቱ ኅዳር ወር ሲጠባ፣ አዲስ አበባ በልዩ ድምቀት፣ በማይቆም የአረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ጎርፍ ትናወጣለች። ከ25 ዓመታት በፊት በጀግናው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ራዕይ የተጀመረው “ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ” ዛሬ ላይ 26ኛ ዓመቱን ሲያከብር፣ ከ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር በላይ የአፍሪካ ትልቁ የጎዳና ላይ የሩጫ ፌስቲቫል እና ሌላኛው የመዲናችን ድምቀት ሆኖ ቀጥሏል።
ይህ ታላቅ መድረክ ኢትዮጵያ በረጅም ርቀት ሩጫ ያላትን የማይደፈር ዓለም አቀፍ ዝና ከዘመናዊቷ አዲስ አበባ ገጽታ እና ከሕዝቦቿ የእንግዳ ተቀባይነት ባህል ጋር በማስተሳሰር፣ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አዲስና ብሩህ የኢትዮጵያን ገጽታ የሚያሳይበት ወርቃማ አጋጣሚ ነው።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የስፖርት መድረክ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚታወሰው በረጅም ርቀት ሩጫ ያስመዘገበችው አስደናቂ ታሪክ ነው።
ከአበበ ቢቂላ የሮም ባዶ እግር ድል ጀምሮ እስከ ምሩጽ ይፍጠር፣ ደራርቱ ቱሉ፣ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ጥሩነሽ ዲባባ እንዲሁም ዛሬ ላይ የዓለምን ክብረወሰኖች እየሰባበሩ እስከሚገኙት አዳዲስ ትውልዶች እነ ትዕግሥት አሰፋ፣ ጉዬ አዶላ፣ ልቅና አምባው፣ ጉዳፍ ፀጋይ እና ለተሰንበት ግደይ ድረስ፤ አትሌቲክስ ለኢትዮጵያውያን ከስፖርትም በላይ የማንነት መገለጫ እና የብሔራዊ ኩራት ምንጭ ነው።
26ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ይህንን ታሪካዊ ቅርስ ለትውልድ የሚያስተላልፍበት ሕያው መድረክ ነው። ውድድሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑ የኢትዮጵያ ጀግኖች አትሌቶች፣ ወጣት ተተኪዎች እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪዎች በአንድ ጎዳና ላይ የሚገናኙበት ነው።
ይህም አዲስ አበባን የዓለም የረጅም ርቀት ሩጫ መናኸሪያ መሆኗን በድጋሚ የሚያረጋግጥና የኢትዮጵያን የአትሌቲክስ የበላይነት ለዓለም የሚያሳይ ትዕይንት ነው።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን ከሌሎች ዓለም አቀፍ የማራቶን እና የጎዳና ላይ ውድድሮች ልዩ የሚያደርገው፣ በውድድሩ ዕለት የሚታየው ሕዝባዊ ስሜትና ደማቅ ድባብ ነው።
በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች ተመሳሳይ የመሮጫ ቲ-ሸርት ለብሰው በአንድ ልብ ሲሮጡ፤ የዕድሜ፣ የፆታ፣ የቋንቋ ወይም የማኅበራዊ ደረጃ ልዩነቶች ጠፍተው አንድ ወጥ የሆነ ኢትዮጵያዊ አብሮነት ይንጸባረቃል።
ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚመጡ ሯጮችና ጎብኚዎች በኢትዮጵያውያን የሚደረግላቸው ሞቅ ያለ አቀባበል፣ በመንገድ ዳር ቆመው በጭብጨባና በእልልታ የሚያበረታቱ ነዋሪዎች ፈገግታ፣ የኢትዮጵያውያንን የእንግዳ ተቀባይነት እሴት በተግባር ያሳያል።
ይህም ታላቁ ሩጫን “የዓለም እጅግ አስደሳች ውድድር” የሚል ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኝ አስችሎታል።
የዘንድሮው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የሚካሄደው አዲስ አበባ በከፍተኛ የከተማ ልማትና የመሠረተ ልማት ለውጥ ውስጥ በምትገኝበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ነው።
የታላቁ ሩጫ ተሳታፊዎች በእነዚህ ውብና ዘመናዊ ጎዳናዎች ላይ ሲሮጡ፣ ውድድሩ የከተማዋን አዲስ የልማት ምዕራፍ ለዓለም መገናኛ ብዙኃንና ለውጭ እንግዶች በቀጥታ የሚያስተዋውቅ መስኮት ይሆናል።
ንጹሕ፣ አረንጓዴ እና ለነዋሪዎቿም ሆነ ለጎብኚዎቿ ምቹ የሆነችዋን አዲስ አበባ በቴሌቪዥን መስኮቶችና በማኅበራዊ ሚዲያዎች ለሚመለከቱ ሚሊዮኖች፣ ኢትዮጵያ በለውጥ ጎዳና ላይ የምትገኝ ዘመናዊ ሀገር መሆኗን በግልጽ ያሳያል።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለሀገራችን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ እና ለከተማዋ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከፍተኛ የሆነ የገቢና የሥራ ዕድል መነቃቃትን ይፈጥራል። ውድድሩን ምክንያት በማድረግ በሺዎች የሚቆጠሩ ዓለም አቀፍ አትሌቶች፣ የስፖርት ቱሪስቶች፣ ጋዜጠኞች እና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ወደ አዲስ አበባ ይጎርፋሉ።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም የኢትዮጵያን ትናንት፣ ዛሬ እና ነገ በአንድ መድረክ የሚያገናኝ ታላቅ ብሔራዊ ትዕይንት ነው።
የትናንቱን የአትሌቲክስ ጀግንነት ከዛሬው የአዲስ አበባ ዘመናዊ የከተማ ልማት እና ከሕዝቦቿ ዘመን ተሻጋሪ የእንግዳ ተቀባይነት ባህል ጋር በማዋሐድ፣ ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የምታቀርበው የሰላም፣ የአብሮነትና የብልጽግና መልዕክት ነው።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: