Search

አፍሪካ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በጋራ ለመከላከል በትብብርና በቅንጅት መሥራት ያስፈልጋታል

ቅዳሜ ኅዳር 12, 2019 104

በአፍሪካ እየተስፋፉ የመጡትን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ለመከላከል በቂ የፖለቲካ ቁርጠኝነት፣ ዘላቂ የገንዘብ ድጋፍ እና በአህጉር አቀፍ ደረጃ የተቀናጀ አመራር እንደሚያስፈልግ ተገለጸ።

የጤና ሚኒስቴር ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ከተውጣጡ የጤና መሪዎች፣ የተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ጥምረት ተወካዮች እና ባለሙያዎች ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ በአፍሪካ የበሽታዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል በተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ላይ ያተኮረ ውይይት እያካሄደ ይገኛል።

የአፍሪካ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ኔትወርክ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ካውሺክ ራማያ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ሥርጭት በአህጉሪቱ እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመዋል።

አፍሪካውያን ችግሩን ለመግታት በቅንጅትና በትብብር መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበው፣ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ የበርካታ ዜጎችን ሕይወት እየቀጠፉ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የአፍሪካ አሁን ባለችበት ሁኔታ ከቀጠለች፣ እስከ ፈረንጆቹ 2030 ከእነዚህ በሽታዎች ጋር በተያያዘ የሚከሰተውን የዜጎቿን የሞት ምጣኔ ለመቀነስ የያዘችውን ዕቅድ ማሳካት አስቸጋሪ እንደሚሆንባት አስጠንቅቀዋል።

በውይይቱ ላይ ሀገራት ከጤና ጋር የተያያዙ የታክስ ፖሊሲዎችን ማጠናከርና ከዓመታዊ በጀታቸው ለጤና የሚመድቡትን የፋይናንስ ድርሻ ማሳደግ እንደሚገባቸው ተመላክቷል።

በተጨማሪም አፍሪካ በጤናው ዘርፍ ራሷን ችላ እንድትቆምና በውሳኔ ሰጪነት የጤና ሉዓላዊነቷን እንድታረጋግጥ፣ የጤና ፋይናንስና የፖሊሲ አጀንዳዎች በለጋሽ ሀገራት ሳይሆን፣ በአፍሪካ ፍላጎትና ቅድሚያ በሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ የተመሠረቱ እንዲሆን የሚያስችል ሥርዓት መገንባት እንደሚገባ ተገልጿል።

የአፍሪካ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ሕብረቶችም ከቃል ኪዳን ወደ ተግባራዊ እርምጃ እንዲሸጋገሩ ጥሪ ቀርቧል።

ኢትዮጵያ በመጪው ሰኞ ከምታስጀምረው አህጉር አቀፍ ጉባኤ አስቀድሞ የተዘጋጀው ይህ ውይይት፣ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን በቆይታውም የአፍሪካ ሀገራት እየተስፋፉ የመጡትን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ለመከላከል የሚያስችል ሰፊ የልምድና የዕውቀት ልውውጥ እንደሚያደርጉበት ይጠበቃል።

በመሃሪ  ዓለሙ

 

 

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: