የኢትዮጵያ ሕልውና፣ ልዕልና እና ታሪካዊ መስተጋብር ከሁለት ታላላቅ ውኃዎች ጋር በእጅጉ የተጋመደ ነው።
አንደኛው ከራሷ ማኅፀን ፈልቆ በረሃውን የሚያለመልመው ዓባይ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ታሪካዊ ስሟም ሆነ አካሏ የማይነጠል ቀይ ባሕር ነው።
እነዚህ ሁለቱ ውኃዎች የኢትዮጵያ ታሪክ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፤ ዓባይን ያለ ቀይ ባሕር፣ ቀይ ባሕርን ያለ ኢትዮጵያ ማንሣት እንደ ግንጥል ጌጥ የሚቆጠረውም ለዚሁ ነው።
ለዘመናት በውኃ የተከበበች ዓሣ ነባሪ በውኃ ጥም እንደምትቸገር ሁሉ፣ ኢትዮጵያም የራሷን የውኃ ሀብት መጠቀም እንደ ነውር፣ የባሕር በር ባለቤትነቷን ደግሞ እንደ ዝግ አጀንዳ እንድትቆጥር ተደርጋ ኖራለች።
ሆኖም ይህ "አይቻልም" የሚለውን የሥነ-ልቦና ስብራት ታላቁን የሕዳሴ ግድብ በመገንባት ቀልብሳዋለች። የዓባይ ውኃ የኛ ነው ሲሉ ጠብታ ውኃ እንኳ ያላበረከቱት ሀገራት የፈጠሩትን ተፅዕኖ በጣጥሳ፣ ይሉኝታን አውልቃ በመጣል ብሔራዊ ጥቅሟን አስጠብቃለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዚህን ስትራቴጂያዊ ውኃ ትርጉም በተመለከተ ሲገልጹ፣ ሕዳሴ የትናንት ቁጭት ማሳያ፣ “የመጪው ዕድገት ማብሰሪያ ነው” በማለት በዓባይ ላይ የተገኘው ድል የመጪው ተስፋ መሠረት መሆኑን አብራርተዋል።
ይህ በአንደኛው ውኃ (ዓባይ) ላይ የተገኘው ሀገራዊ ድል እና የትናንት ቁጭት ማካካሻ፣ ዐይኑን ወደ ሁለተኛው ውኃ ይኸውም ወደ ቀይ ባሕር ማዞሩ የአጋጣሚ ጉዳይ አይደለም፤ ይልቁንም የተፈጥሮ እና የታሪክ ግዴታ ነው።
130 ሚሊዮን ሕዝብ ይዛ እና ግዙፍ የኢኮኖሚ አቅም ፈጥራ ያለ ባሕር በር ተዘግታ የምትኖርበት ምንም ዓይነት ጂኦ-ፖለቲካዊም ሆነ ሞራላዊ ምክንያት የለም። ይሁንና ኢትዮጵያ ከዚህኛው ውኃ እንድትርቅ የተደረገው በታቀደ ስትራቴጂያዊ ሴራ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ያዕቆብ ኃይለማርያም (ዶ/ር) ‘አሰብ የማን ናት?’ በሚለው መጽሐፋቸው የጂኦ-ፖለቲካውን ሴራ ሲያጋልጡ፣ የኢትዮጵያ የባሕር በር እጦት የውጭ ኃይሎች የረጅም ጊዜ የመነጠል ፖለቲካ ውጤት መሆኑን ያስገነዝባሉ። ታሪካዊ ጠላቶቻችን ኢትዮጵያን በማግለል ቀይ ባሕርን ለመቆጣጠር የነበራቸውን የረጅም ጊዜ ዓላማ በሴራ አሳክተዋል ይላሉ ዶ/ር ያዕቆብ።
የቀይ ባሕር እና የኢትዮጵያ ቁርኝት የኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን የደም፣ የማንነት እና የታሪካዊ ይዞታ ጉዳይ ነው። ጥንታዊው የአክሱም ሥልጣኔ የገነነው በአዱሊስ ወደብ አማካኝነት በነበረው የባሕር ላይ ተሳትፎ ሲሆን ትናንትም ሆነ ዛሬ የባሕሩ ዳርቻ የኢትዮጵያውያን ታሪካዊ መኖሪያ ነው።
የኢትዮጵያ ምሥራቃዊ ወሰን የቀይ ባሕርን ዳርቻ (የአፋሩን የሱልጣን ሃንፋሬን ግዛት) አጠቃልሎ አረፋሊ እንደሚደርስ ማስረጃ የጠቀሱት ዶ/ር ያዕቆብ፣ ኢትዮጵያ ከሁለተኛው ውኃ ጋር ያላት ትሥሥር በማይፋቅ የታሪክ መዝገብ የሠፈረ መሆኑን አበክረው ያብራራሉ።
በመሆኑም የኢትዮጵያ የዕጣ ፈንታ ጉዞ የተቋጠረው በእነዚህ ሁለት ውኃዎች መዳፍ ላይ ነው። በዓባይ ወንዝ ላይ የተገነባው የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በጋራ ከቆሙ የውኃ ሀብታቸውን ወደ ብልጽግና መቀየር እንደሚችሉ ያስመሰከረ ነው።
ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር በቀረበች ቁጥር የማንም ስጋት የማትሆን ይልቁንም ቀጣናው በሩቅ ኃያላን ሀገራት የጦር መርከቦች እየታመሰ እና የጂኦ-ስትራቴጂያዊ መሻኮቻ በሆነበት በአሁኑ ወቅት፣ የኢትዮጵያ መራቅ የሚያመጣው ሰላም የለም፤ መቅረቧ ግን የሚያረጋግጠው ቀጣናዊ መረጋጋት እና የኢኮኖሚ ትሥሥር ይኖራል።
ጊዜው የአዲሱ የመደመር ትውልድ ነው። ከታሪክ ስህተት በመማር፣ ለ30 ዓመታት እንደ ነውር ሲቆጠር የቆየውን የቀይ ባሕር የባለቤትነት ጥያቄ ከቁጭት ወዳለፈ ሀገራዊ አጀንዳነት አሸጋግሮታል።
የኢትዮጵያ ልዕልና ሙሉ የሚሆነው አንደኛውን ውኃ (ዓባይ) በሕዳሴ ግድብ እንዳበራችው ሁሉ፣ ሁለተኛውን ውኃ (ቀይ ባሕር) ደግሞ በሰላማዊ፣ ሕጋዊ እና አስተማማኝ የዲፕሎማሲ መንገድ ተደራሽ ማድረግ ስትችል ነው።
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: