Search

የዘመናት ሴራ እና ከበባን የሰበረ ትውልድ፦ ከሄሮዶተስ እስከ ዓባይ ግድብ እና ቀይ ባሕር መዳረሻ

ሓሙስ ነሐሴ 28, 2018 119

የታሪክ አባት በመባል የሚታወቀው ግሪካዊው ሄሮዶተስ "ግብጽ የዓባይ ስጦታ ናት" ብሎ ሲጽፍ፣ የዚህ ታላቅ ስጦታ ብቸኛ ምንጭ የሆነችው ኢትዮጵያ ስውር የጂኦ-ፖለቲካ ሴራ ተተብትባ እንድትቆይ ተፈርዶባት ነበር።

"የውኃ ማማነት" ሲወሳ ለዘመናት በበጎ ስናነሳው የቆየ እና በውስጡ ግን አደገኛ እና አሉታዊ ትርክትን ያዘለ ነበር። "የውኃው ትክክለኛ ባለቤት ግብጽ ናት" የሚል የሥነ-ልቦናዊ ዕሳቤን በማስረጽ፣ ሀገራችን ውኃዋን ከማፍሰስ ባለፈ ተጠቃሚ እንዳትሆን የተቀመረ የሴራ ትንተና ሆኖ ቆይቷል።

ይህ የዘመናት ሴራ ሃይማኖትን እና የፈጠራ ትርክቶችን እንደ ዋነኛ ማስፈጸሚያ ተጠቅሟል። ለዘመናት ግብጽ ጳጳሳትን ወደ ኢትዮጵያ ስትልክ የነበረው፣ መንፈሳዊ የበላይነትን ለማራመድ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ታሪካዊ ትርክት በግብጻውያን ሞግዚትነት ሥር እንዲወድቅ ለማድረግ ጭምር ነበር።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በአውሮፓውያን ዘንድ በሰፊው ይናፈስ የነበረው "የፕሪስተር ጆን" (Prester John) አፈ ታሪክ የዚሁ መገለል ተያያዥ አካል ሆኖ አገልግሏል። ይህ ትርክት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ተጨባጭ የጂኦ-ፖለቲካዊ ተዋናይ እና የውኃ ባለቤት ከመሆን ይልቅ፣ ከተቀረው ዓለም የተገለለች፣ በተራራ ላይ የተደበቀች ምሥጢራዊት ምድር (Mythical Land) ተደርጋ እንድትሳል አድርጓል።

በዚህ የረጅም ጊዜ ስትራቴጂ እና ሥነ-ልቦናዊ ጫና ምክንያት፣ የውኃ ባለቤት የሆኑት ታላላቆቹ የኢትዮጵያ ሥልጣኔዎች ከባሕር ዳርቻዎች፣ ከወንዞች እና ከውኃማ አካባቢዎች ቀስ በቀስ እየተገፉ በተራራ ላይ ብቻ እንዲሰፍሩ ሆኗል።

ኢትዮጵያውያን የባሕር ኃይል፣ የውኃ ላይ ንግድ እና የዘመናዊ ግብርና ባለቤት እንዳይሆኑ በመደረጉ፣ የውኃ ዳር ሰዎች መሆናቸው ቀርቶ የተራራ እና የኮረብታ ሕዝብ ብቻ ተደርገው እንዲወሰዱ ተሠራ። ሀገራችን የራሷን የውኃ ባለቤትነት ትርክት የማዳበር አቅሟን እንድታጣ፣ ቆላማው ክፍሏ ደግሞ የጦርነት እና የግጭት ቀጣና ብቻ እንዲሆን ሆን ተብሎ ተሴረ።

ዘመናት ተቆጥረው ወደ ዐሥራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ስንሻገር፣ በአሜሪካ በተነሣው የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት በእንግሊዝ ከፍተኛ የጥጥ አቅርቦት እጥረት ተከሰተ። በዚህ ጊዜ እንግሊዞች ፊታቸውን ወደ ግብጽ ሲያዞሩ፣ የእስማኤል ፓሻ መንግሥት የእንግሊዞችን የጥጥ እርሻ ማስፋፋት ፕሮጀክት እውን ለማድረግ ሲል እጅግ ከፍተኛ የሆነ የውኃ እና የመሬት ጥማት ውስጥ ገባ። የጥጥ ኢምፔሪያሊዝምን ለማስፋፋት ሲባል ብቻ የኢትዮጵያን ለም የቆላማ መሬቶች፣ የኤርትራን አዋሳኝ ስፍራዎች፣ እንዲሁም የዓባይን ምንጭ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ግድ አላቸው።

ይህንን ሕልም ለማሳካት እስማኤል ፓሻ ሰላዮችን በነጋዴ እና በአሳሽ ስም ወደ ኢትዮጵያ በስፋት አሰማራ። ከእነዚህም መካከል ስዊዘርላንዳዊው ቨርነር ሙንዚንገር ዋነኛው ነበር። ሙንዚንገር የኢትዮጵያን ሰሜናዊ ክፍል አጥብቆ በመሰለል፣ የውኃ መገኛዎችን እና የንግድ መስመሮችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ታላቅ ሴራ ጠነሰሰ። ሴራው በስለላ ብቻ አላበቃም፤ ኢትዮጵያን በሁሉም አቅጣጫ ወደሚያዳክም መጠነ ሰፊ የከበባ ጦርነት ተሸጋገረ።

ግብጻውያን ምጽዋን እና ቀይ ባሕርን በመቆጣጠር ከሰሜን፣ በሱዳን በኩል መተማን በመያዝ ከምዕራብ፣ እንዲሁም በራኡፍ ፓሻ አዛዥነት ሐረርን በመውረር ከደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ የከበባ ቀለበት ውስጥ አስገቧት። ከዚህም ባለፈ የውስጥ ባላባቶችን በማጋጨት ሀገራችን የውክልና ጦርነቶች ሰለባ እንድትሆን አደረጉ።

ነገር ግን፣ ከሄሮዶተስ "ግብጽ ስጦታ" እና "ውኃ ማማነት" ሥነ-ልቦናዊ ወጥመድ እስከ "ፕሪስተር ጆን" የብቸኝነት አፈ ታሪክ፣ እንዲሁም እስከ እስማኤል ፓሻ የጥጥ እርሻ እና ወታደራዊ ወረራ ድረስ የተዘረጋው ይህ ረጃጅም የሴራ ሰንሰለት ዛሬ ላይ ግብዓተ መሬቱ ተፈጽሟል።

ዘመናዊቷ ኢትዮጵያ እና የዛሬው ጀግና ትውልድ ይህንን የዘመናት ስብራት እና የዙሪያ ከበባ በጽናት ሰብረው ወጥተዋል።

"ማማ ብቻ ሆናችሁ ውኃውን አሳልፉ" የሚለውን የዘመናት የተንሸዋረረ ትርክት በመቀልበስ፣ የዛሬው ጀግና ትውልድ በራሱ አቅም እና ላብ ታላቁን የሕዳሴ ግድብ ገንብቶ ዓባይን በመገደብ ታሪካዊ መብቱን በተግባር አረጋግጧል። ኢትዮጵያ ውኃን ጠባቂ ማማ ብቻ ሳትሆን፣ የውኃዋ ፍጹም ባለቤት እና ተጠቃሚ መሆኗን ለዓለም በተጨባጭ አሳይታለች።

ከዚህም ባለፈ፣ ለዘመናት ከተራራ ሕዝብነት እንዳትወጣ እና ከውኃ እንድትርቅ የተደረገችው ኢትዮጵያ፣ ዛሬ ያንን ጂኦግራፊያዊ እና ፖለቲካዊ መገለል ሰብራ ወደ ቀይ ባሕር ዳርቻዋ መመለስ ጀምራለች። የባሕር በሯን መልሳ ለማግኘት እና የውኃ ላይ ጂኦ-ፖለቲካዊ ተጽዕኖዋን ለማረጋገጥ የምታደርገው ጥረት፣ ሀገራችን ከተጫነባት "የተራራ ላይ ብቻ መታጠር" ሴራ ሙሉ በሙሉ ነጻ እየወጣች መሆኗን የሚያበስር ታሪካዊ እርምጃ ነው።

የዓባይ መገደብ እና ወደ ቀይ ባሕር የመጠጋቱ ስትራቴጂያዊ ጉዞ፣ ኢትዮጵያ የዘመናት ሴራዎችን ቀዳዳ ደፍና ወደ ትክክለኛ ታሪካዊ፣ ጂኦግራፊያዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ከፍታዋ እየተመለሰች መሆኗን የሚያረጋግጥ ሕያው ምሥክር ነው!

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: