ሀገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በየዘርፉ የምታስመዘግባቸው ሁለንተናዊ ስኬቶች እና የብልጽግና ማሳያዎች መካከል የሀገር ውስጥ ገቢ አሰባሰብ እና የታክስ ሥርዓት ትራንስፎርሜሽን በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።
የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እና ግዙፍ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም ለመሸፈን በሚደረገው ጥረት፣ የገቢ አሰባሰብ አቅምን ከቢሊዮን ወደ ትሪሊዮን ብር ማደጉ ትልቅ ታሪካዊ ምዕራፍ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ2018 በጀት ዓመት ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፣ ሀገራችን ባለፉት 27 ዓመታት በአጠቃላይ የሰበሰበችው ገቢ 1 ትሪሊዮን ብር እንኳን የማይሞላ የነበረ ቢሆንም፣ በ2018 በጀት ዓመት ብቻ ግን 1.5 ትሪሊዮን ብር ገቢ በመሰብሰብ ከ150% በላይ ታሪካዊ ብልጫ ያለው እመርታ ማስመዝገብ ተችሏል።
ይህ የገቢ ማደግ እንደ ኮሪደር ልማት፣ የትምህርትና ጤና መሰረተ ልማቶች እንዲሁም የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን በራስ አቅም ለመሸፈን የሚያስችል ጠንካራ የፋይናንስ ነፃነት እና ኢኮኖሚያዊ መሰረት ፈጥሯል።
ለዚህ ታሪካዊ የገቢ እድገት እና እመርታ ዋናው ስኬት የግብር አሰባሰቡን አሠራር በዲጂታል ቴክኖሎጂ ማደራጀት እና ማዘመን ነው።
በሀገራችን የተጀመረው የኤሌክትሮኒክ ታክስ (ኢ-ታክስ) አጠቃቀም በስፋት ሥራ ላይ በመዋሉ ግብር ከፋዩ ኅብረተሰብ በየቢሮው በሰልፍ ያሳልፍ የነበረውን ጊዜና ወጪ በመቀነስ ባሉበት ሆነው በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ የታክስ ማሳወቂያ እንዲያቀርቡና ክፍያቸውን እንዲፈጽሙ አስችሏል።
ይህ አሠራር የአካል ንክኪንና ባህላዊ ቢሮክራሲን በማስቀረት የታክስ ስወራን፣ መዘግየቶችን እና ህገ-ወጥ አሠራሮችን በእጅጉ ቀንሷል።
የፖስ እና የኢ-ኮመርስ አሠራሮችን በቀጥታ ከገቢዎች ሚኒስቴር የመረጃ ቋት ጋር ማያያዝ መቻሉ በስርዓቱ ላይ ግልጽነትን የፈጠረ ሲሆን፣ ነጋዴውና ባለሀብቱ በታክስ ሂደቶች ላይ ያባክኑ የነበረውን ጉልበት ወደ ዋናው የምርታማነት ሥራቸው እንዲያዞሩ በማድረግ ለሀገር ውስጥ ምርት ማደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል።
ከዲጂታል አሠራር ጎን ለጎን የግብር አሰባሰቡን በህግ ከማስገደድ ይልቅ በፈቃደኝነት ላይ ወደተመሰረተ የታክስ ባህል ማሸጋገር መቻሉ ሌላው እመርታ ነው።
ቀደም ሲል በግብር ሰብሳቢው እና በግብር ከፋዩ መካከል የነበረውን በፍርሃትና በጥርጣሬ የተሞላ ግንኙነት በመቀየር፣ ህዝባዊ ንቃተ-ህሊናን የሚያሳድጉ የዲጂታል ሚዲያ ዘመቻዎች፣ የምክክር መድረኮች እና በትምህርት ካሪኩለም ውስጥ የታክስ እውቀትን ማካተት የተቻሉ ስራዎች ተከናውነዋል።
ታማኝና ከፍተኛ ግብር ከፋዮችን በጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ ማሸለም አዎንታዊ ውድድርን የፈጠረ ሲሆን፣ ህዝቡም ገቢዎች ሚኒስቴርን የጋራ ሀብት አስተዳዳሪ አድርጎ የመመልከትና በራሱ ፍላጎት ግብሩን የማወጅ ልምዱ አድጓል።
በተጨማሪም የታክስ መሠረቱን በማስፋት፣ አዳዲስ የንግድ ዘርፎችን ወደ ፋይናንስ ሥርዓቱ በማስገባት እና ህጋዊ የሽያጭ ደረሰኝ የመጠየቅ ባህል እንዲጎለብት በማድረግ አስተማማኝ የገቢ መሠረት ተጥሏል።
ይህንን የታክስ እና የገቢ እመርታ ሙሉ ለማድረግ የኮንትሮባንድ ንግድ ቁጥጥር እና የጉምሩክ አሠራር ዘመናዊነት ከፍተኛ ድርሻ ተጫውተዋል።
እንደ ቡና፣ ሰሊጥ፣ ወርቅ እና የቀንድ ከብቶች ያሉ ስትራቴጂካዊ ምርቶች በህገ-ወጥ መንገድ እንዳይወጡ በማድረግ ሀገር ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝ ተደርጓል።
በሌላ በኩል በጉምሩክ ኬላዎች ላይ የኤክስሬይ ስካነሮችን፣ የካርጎ ክትትል ቴክኖሎጂዎችን እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት የተደገፉ የፍተሻ ዘዴዎችን በመተግበር ህገ-ወጥ እቃዎችን በመቆጣጠር የሀገር ውስጥ አምራቾች ተጠብቀዋል።
የጉምሩክ ኮሚሽን ከአንድ መስኮት አገልግሎት እና ከባለብዙ አማራጭ ሎጂስቲክስ አውታር ጋር በመቀናጀት የድንበር ንግድን በማፋጠን የሀገራችንን የንግድ ተወዳዳሪነት አሳድጓል።
እነዚህ የተቀናጁ የገቢ፣ የታክስ፣ የዲጂታላይዜሽን እና የጉምሩክ ማሻሻያዎች ኢትዮጵያ በፅኑ መሰረት ላይ የቆመች እና በራስ አቅም የምትመራ የበለጸገች ሀገር ለመሆን ያደረገችውን ታሪካዊ የእመርታ ጉዞ በግልጽ ያሳያሉ።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: