Search

ከላቦራቶሪ እስከ የእናትነት ጽናት፤ የጽናት ለገሰ ድንቅ የፈጠራ ጉዞ

ቅዳሜ ኅዳር 12, 2019 114

በሳይንስ፣ በምርምርና በፈጠራ ዓለም ስምና ዝና ሲጠቀስ ብዙውን ጊዜ የወንዶች ታሪክ ቀድሞ ቢመጣም፣ ዘመናዊ ሳይንስና ፈጠራ ዛሬ ለደረሱበት ደረጃ የሴቶች አስተዋፅዖም የማይነጣጠል መሠረት ነው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ “ራዲየም” የተሰኘውን ንጥረ ነገር ያገኘችው ማሪ ኩሪ እና የዘረመል (DNA) አወቃቀርን ለመረዳት የሚያግዙ ወሳኝ ምስሎችን ያበረከተችው ሮዛሊንድ ፍራንክሊን ለዚህ ዋነኛ ማሳያዎች ናቸው።

በኢትዮጵያም የመጀመሪያዋ ሴት ፕሮፌሰር ዓለምፀሐይ መኮንን እና በዕፅዋት በሽታ ጥናት የሚታወቁት ዶ/ር ሰገነት ቀለሙ የዚህ ታሪካዊ የዕውቀት ሰንሰለት አካላት ናቸው። ዛሬ የእነዚህን ድንቅ እንስቶች ፈለግ በመከተል፣ ጽናት ለገሰ ከአኩሪ አተርና ከሌሎች ጥራጥሬዎች የተቀመመ የፕሮቲን ዱቄት በማዘጋጀት የራሷን ታሪክ እየጻፈች ትገኛለች።

ጽናት በቅርቡ በተካሄደው የአምስተኛው ዙር “የነጋድራስ” የሥራ ፈጠራ ውድድር የአንድ ሚሊዮን ብር አሸናፊ ስትሆን፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክም የፈጠራ ሥራዋን ለማስፋፋትና ለማሳደግ ያለዋስትና የ10 ሚሊዮን ብር ብድር ታገኛለች።

የውድድሩ አሸናፊዋ ጽናት ከኢቢሲ ጋር ባደረገችው ቆይታ እንደገለጸችው፣ የፈጠራ ሥራዋ ዋነኛ መነሻ የማስተርስ ጥናቷን ለማካሄድ ከአዲስ አበባ ውጪ ወጥታ ያየችው የአርሶ አደሮች ሕይወት ነው።

የሁለት ልጆች እናት እና የ“ሶራ የምግብ ማኑፋክቸሪንግ” ስታርታፕ መሥራች የሆነችው ጽናት፣ የመጀመሪያ ዲግሪዋን በባዮሎጂ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ሁለተኛ ዲግሪዋን ደግሞ በጄኔቲክስ (ዘረመል) ከወሎ ዩኒቨርሲቲ በከፍተኛ ማዕረግ አጠናቅቃለች።

በመቀጠልም በጂንካ ዩኒቨርሲቲ ተመድባ ለአምስት ዓመታት በመምህርነት ማገልገሏን ተከትሎ፣ በግል ላቦራቶሪ ውስጥ ለሁለት ዓመታት በመሥራት የምርምር ልምዷን አጠናክራለች።

ሙያዊ ሕይወትን ከቤተሰብ ኃላፊነት ጋር ማስማማት ለብዙ ሴቶች ፈተና እንደሆነ ሁሉ፣ ጽናትም የሁለት ልጆች እናት በመሆኗና የቤተሰብ ኃላፊነት ስለበዛባት መደበኛ ሥራዋን ለመተው ተገዳ ነበር።

ይሁን እንጂ ለልጆቿ እንክብካቤ የቤት እመቤት በሆነችባቸው ሁለት ዓመታት ውስጥ ጥናቷን አላቋረጠችም፤ ይልቁንም የሳይንስ ዕውቀቷን የሚያሳድጉ ጥናቶችን ቀጥላለች። በዚህ ወሳኝ የሽግግር ወቅት የባለቤቷ መላኩ ማቴዎስ ያላሰለሰ ድጋፍና የቤተሰቦቿ ከጎኗ መቆም ትልቅ ብርታት ሆኗታል።

የሳይንስ ዕውቀትን በላቦራቶሪ ውስጥ ብቻ ከማቆየት ይልቅ ከማኅበረሰቡ ዕለታዊ ፍላጎት ጋር ማገናኘት አለብኝ የምትለው ጽናት፣ የ“ሶራ ፕሮቲን” ሐሳብ የመነጨው የኢትዮጵያን የጥራጥሬ ሀብት ለመመዝገብ በወጣችበት የማስተርስ የመስክ ሥራ ወቅት እንደሆነ ተናግራለች።

ከአርሶ አደሩ ጋር በአካል ተገናኝታ ባደረገችው ምልከታ፣ የሀገራችንን ሰፊ የጥራጥሬ ሀብት ወደ ተጨማሪ የምግብ እሴት የመቀየር ክፍተት በተለይም የሥጋና የእንቁላል ዋጋ እንዲሁም የሕፃናት የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በምግብ ፈጠራ ላይ እንድታተኩር አነሳስቷታል።

በሳይንሳዊ መንገድ በባቄላ፣ በሽምብራ፣ በአኩሪ አተርና በሌሎች ጥራጥሬዎች ውስጥ የሚገኙ ንጥረ ምግቦችን ሊገድቡ የሚችሉ ፀረ-ንጥረ ምግቦችን (Anti-nutrients) ለመቀነስ “Sprouting” የተሰኘውን ዘዴ በመጠቀም፣ አኩሪ አተርንና ሌሎች የሀገር ውስጥ ጥራጥሬዎችን በማቀናጀት “ሶራ” የተሰኘውን የፕሮቲን ዱቄት አዘጋጅታለች።

ስያሜው በሲዳምኛ እና በተለያዩ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች “ምግብ” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን፣ በላቦራቶሪ ምርመራና በኢትዮጵያ ጥራትና ምዘና ድርጅት መለኪያ መሠረት ምርቱ 48 ግራም ፕሮቲን፣ ወደ 50 ሚሊግራም ብረት (Iron)፣ 21 ግራም ካርቦሃይድሬት እንዲሁም ወደ 23 ግራም ስብ መያዙ ተረጋግጧል።

የሳይንስ ግኝትን ወደ ገበያ ሊቀርብ የሚችል ምርት መቀየር የንግድ ዕውቀትንና የፋይናንስ አቅምን ስለሚጠይቅ፣ ጽናት በሥራ-ፈጠራ ዕድገት ኢንስቲትዩት የሥራ ፈጠራ ሥልጠና ከመውሰዷ ባሻገር የንግድ መጻሕፍትን በማንበብ ራሷን አብቅታለች።

በአሁኑ ወቅት የሶራ ፕሮቲን ዱቄት በአነስተኛ የጎጆ ኢንዱስትሪ ደረጃ እየተመረተ በሀገር ውስጥ ገበያ እየቀረበ ሲሆን፣ በቀጣይ 5 ዓመታት ውስጥ በአፍሪካ የመጀመሪያው የፕሮቲን አምራች ድርጅት ለማድረግ እና የሕፃናት መቀንጨርን ለመቀነስ ትልቅ ራዕይ ሰንቃለች።

የጽናት ለገሰ ጉዞ የምርምር ዕውቀት ከላቦራቶሪ ግድግዳ ወጥቶ፣ በቤተሰብ ድጋፍና በጠንካራ ጽናት ሲታገዝ እንዴት ወደ ተጨባጭ ሀገራዊ ሀብትና ሥራ ፈጠራ እንደሚቀየር የሚያሳይ ሕያው ምሳሌ ነው። ጽናት የሥራ ፈጠራ ውድድር አሸናፊ እንድትሆን ዕድሉን ላመቻቹት ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምስጋና አቅርባለች።

በልዩ እሸቱ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: