የ2019 ዓ.ም አዲስ ዓመትን ስንቀበል ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ እና በመሠረተ ልማት ግንባታ ላይ ጠንካራ መሠረት ጥላ ከማንሠራራት ወደ ተጨባጭ ዕድገት እየተሸጋገረች ነው።
ይህንን ሀገራዊ ራዕይ ዕውን ለማድረግ የሲሚንቶ ምርት አቅርቦትን ማሳደግ እና የገበያ መረጋጋትን ማረጋገጥ ወሳኝ ድርሻ አለው።
በመሆኑም በሥራ ላይ የሚገኙ አምራች ፋብሪካዎችን አቅም ከፍ ለማድረግ ሰፊ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል።
ፋብሪካዎቹ በየጊዜው የሚያጋጥሟቸውን የምርት፣ የግብዓት እና የሥራ አፈጻጸም ችግሮች በቅርበት በመለየት እና በመፍታት በገበያ ላይ የነበረውን የአቅርቦት እጥረት በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ተችሏል።
በአሁኑ ወቅት 12 የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በምርት ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ አዳዲስ ግዙፍ ፋብሪካዎችን ወደ ሥራ የማስገባት ርምጃዎችም ተከናውነዋል።
በቀን 150 ሺህ ኩንታል የማምረት አቅም ያለው ግዙፉ የለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ ለሲሚንቶ አቅርቦት መሻሻሉ ግንባር ቀደም ማሳያ ነው።
የዚህ ግዙፍ ፋብሪካ ወደ ማምረት መሸጋገር በዘርፉ ይፈጠር የነበረውን የአቅርቦት እጥረት እና የዋጋ መዛባት በከፍተኛ ደረጃ አቃልሎታል።
የሲሚንቶ አቅርቦት በተጨባጭ ማደጉ እና በገበያ ላይ መረጋጋት መፈጠሩ በብሔራዊ ደረጃ የሚከናወኑ የካፒታል ፕሮጀክቶች፣ የኮሪደር ልማት ሥራዎች፣ የመንገድና የመኖሪያ ቤቶች ግንባታዎች በዕቅዳቸው መሠረት በፍጥነት እንዲገነቡ አድርጓል።
ይህም የግንባታ ክፍለ-ኢኮኖሚው በአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ላይ ያለው ድርሻ እንዲያድግ እና ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር አስችሏል።
በቀጣይም በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ ያለውን የሲሚንቶ ፍላጎት ለማሟላት እና የተገኘውን ስኬት ይበልጥ ለማጠናከር በግንባታ ላይ ያሉ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ወደ ምርት ለማስገባት እየተሠራ ነው።
በተጨማሪም በነባር ፋብሪካዎች የማስፋፊያ እና የማምረት አቅም ማሳደጊያ ሥራዎችን በማጠናከር አቅርቦቱ በቀጣይነት እንዲሻሻል ሰፊ ራዕይ ተሰንቋል።
ይህ የዘርፉ መነቃቃት የኢትዮጵያ የግንባታ ኢንዱስትሪ እና አጠቃላይ ኢኮኖሚ በቀጣይ ዓመታት ይበልጥ እንደሚያብብ የሚያሳይ ብሩህ ተስፋ ነው።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: