ሀገራችን ኢትዮጵያ የ13ኛዋ ወር ጳጉሜን የመጀመሪያ ቀን የሆነውን የእመርታ ቀን ስታከብር፣ የዓባይ፣ የኦሞ፣ የገናሌ፣ የባሮ እና የአዋሽ መገኛ የመሆኗን ተፈጥሮአዊ ሀብት ወደ እውነተኛ አምራችነት የለወጠችበትን ታሪካዊ የእመርታ ጉዞ በማበሰር ነው።
ለአያሌ ክፍለ ዘመናት የውሃ ሀብቷን መጠቀም ተስኗት፣ ግብርናዋ በዓመት አንድ ጊዜ በሚጥል ዝናብ ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ የኖረ ቢሆንም፣ ባልለፉት ዓመታት በተወሰዱ ስትራቴጂካዊ እርምጃዎች የውሃ ሀብቷን የመጠቀም አቅሟ በከፍተኛ ደረጃ አድጓል።
ከ1960 እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ ባሉት 50 ዓመታት በመስኖ ማልማት የተቻለው 490 ሺህ ሄክታር መሬት ብቻ የነበረ ሲሆን፣ ዛሬ ላይ ግን በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከአምስት እጥፍ በላይ በማሳደግ 2.7 ሚሊዮን ሄክታር ማድረስ ተችሏል።
ይህ በእመርታ ቀን የምናበስረው ታላቅ ስኬት በበጋ ስንዴ ልማት፣ በመስኖ ግድቦች፣ በፓምፕ ቴክኖሎጂዎች እና በወንዝ ጠለፋ ሥራዎች የተመዘገበ ውጤት ነው።
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ይህንን እድገት እንደ መነሻ በመውሰድ የመስኖ ሽፋኑን ወደ 10 ሚሊዮን ሄክታር የማድረስ ግዙፍ ህልም ሰንቆ እየሠራ ይገኛል።
የመስኖ ሽፋኑ 10 ሚሊዮን ሄክታር ሲደርስ የግብርና ምርቱ በሦስት እጥፍ የሚያድግ በመሆኑ፣ በዓመት ሦስት ጊዜ በማምረት ሀገራችን የምግብ ሉዓላዊነቷን ከማረጋገጧ ባለፈ የአፍሪካ የምግብ ቅርጫት እንድትሆን ያስችላታል።
ይህ አብዮት የቴክኖሎጂ ሽግግር ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ የነበራትን የተጎጂነት ሥነ-ልቦና ሰብራ በራሷ እግር የምትቆምበት ታላቅ የኢኮኖሚ መሳሪያ በመገንባቷ፣ የጳጉሜን 1 የእመርታ ቀን አዲሱን የኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነት እና የብልጽግና ዘመን በግልጽ ያበስራል።
በንብረቴ ተሆነ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: