በዛሬው የጳጉሜን 1 የእመርታ ቀን ስናከብር አንዱ መገለጫ በዜጎች አመለካከት ላይ የመጣውን ታሪካዊ የባህል ትራንስፎርሜሽን በማብሰር ነው።
ቀደም ሲል በኢትዮጵያ የነበረው የግብር አሰባሰብ ሂደት በዋናነት በህግ ማስገደድ እና ቁጥጥር ላይ የተመሰረተ በመሆኑ፣ በግብር ከፋዩ እና በገቢ ሰብሳቢው አካል መካከል ያለው ግንኙነት በፍርሃትና በጥርጣሬ የተሞላ ነበር።
ይሁን እንጂ በቅርብ ዓመታት በተደረጉ ስትራቴጂካዊ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ትኩረቱ ወደ ኅብረተሰባዊ ንቃተ-ህሊና ማሳደግ እና በፈቃደኝነት ላይ ወደተመሰረተ የታክስ አሰባሰብ በመቀየሩ በእመርታ ቀን የምናከብረውን ሀገራዊ የአስተሳሰብ እመርታ እውን አድርጎታል።
ይህ በእመርታ ቀን የምናበስረው የባህል ለውጥ የመገናኛ ብዙኃን ዘመቻዎችን፣ የምክክር መድረኮችን፣ በትምህርት ካሪኩለም ውስጥ የታክስ እውቀትን ማካተት እና ታማኝ ግብር ከፋዮችን በጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ ማሸለምን የመሳሰሉ አዎንታዊ ውድድሮችን በመፍጠሩ የተገኘ ውጤት ነው።
ግብር ከፋዮች የደጃፍ ፍተሻ እና ማስገደድ ሳይጠብቁ በራሳቸው ጊዜና ፈቃድ ዲጂታል አማራጮችን በመጠቀም ግብራቸውን የማወጅና የመክፈል ልምዳቸው በከፍተኛ ደረጃ አድጓል።
የኢ-ታክስ አሠራር መዘርጋቱ ሂደቱን በማቃለል፣ ጊዜና ወጪን በመቆጠብ እንዲሁም የሙስና ስጋትን በመቀነስ በሥርዓቱ ላይ ያለው እምነት እንዲጎለብት አድርጓል።
ግብርን እንደ ቅጣት ሳይሆን እንደ ዜግነት ግዴታና ለሀገር ግንባታ እንደሚደረግ ኢንቨስትመንት የመመልከት ባህል መዳበሩ ለሀገራችን የፋይናንስ ነፃነት ወሳኝ ድርሻ ያለው በመሆኑ የጳጉሜን 1 የእምርታ ቀን የኢትዮጵያ የብልጽግና እና የታክስ ባህል ዘመን በግልጽ ያበስራል።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: