Search

የኮንታ ብሔር ዘመን መለወጫ "ህንግጫ" በዓል የባህል እና ቋንቋ ሲምፖዚየም እየተካሄደ ነው

እሑድ ጳጉሜን 01, 2018 174

የኮንታ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል "ህንግጫ" አካል የሆነው ባህልና ቋንቋ ሲምፖዚየም በአመያ እየተካሄደ ይገኛል።

የኮንታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታከለ ተስፉ በሲምፖዚየሙ መክፈቻው ላይ እንደገለጹት፣  ህንግጫ  ከዘመን መለወጫ ባለፈ ሠላም እና ፍቅር  ይበልጥ የሚፀናበት፣ አዲስ ተስፋ እና ፍቅር የሚፈነጥቅበት በዓል ነው።

በዓሉ በብሔሩ ዘንድ ለዘመናት ሲከበር የኖረ፣ ሕዝቦች ራሳቸውን የሚገልጹበት እና ለዘመናት ያዳበሩት ቱባ ባህልና ወግ የሚደምቅበት እንደሆነ ገልጸዋል።

የመደመር መንግሥት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ባህላቸውን ጠብቀው እና አልምተው እንዲጠቀሙ የፈጠረው ምቹ መደላድል በዘርፉ እመርታዊ ለውጦች እንዲመጡ አስችሏል ብለዋል።

የዞኑ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አበበ ደምሴ በበኩላቸው፣ ህንግጫ በብሔሩ ዘንድ ለዘመናት ለዳበረው ማኅበራዊ መስተጋብር አይነተኛ አስተዋጽኦን የሚያበረክቱ እሴቶችን ያዘለ መሆኑን ገልጸዋል።

እሴቶቹም ትውልድን በማነጽ እና ዘላቂ ሠላምና ልማትን በማረጋገጥ ሂደት ከሚያበረክቱት አስተዋጽኦ አኳያ ሕዝባዊ መሠረቱ ጸንቶ እንዲቀጥል ባለድርሻዎችን ያሳተፈ ተግባር እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በህንግጫ በዓል መተጋገዝ በተጨባጭ የሚገለጽበት፣  አብሮነትና አንድነት የሚጎላበት እና ለመጪው ዓመት ተስፋ የሚሰንቅበት  መሆኑን አጽንዖት ሰጥተዋል።

በስምፖዚየሙ የብሔሩ ተወላጆች፣ ምሁራን፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተው የተለያዩ የጥናትና ምርምር ሥራዎች በመቅረብ ውይይት እየተደረገ ሲሆን፣ የብሔሩ ዘመን መለወጫህንግጫበዓል በነገው ዕለት በአደባባይ በተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች እና ዝግጅቶች በድምቀት እንደሚከበር ተገልጿል።

 

በሰለሞን ባረና

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: