ኢትዮጵያ በሁሉም መስኮች ሁለንተናዊ የማንሠራራት ጉዞ መጀመሯን በተጨባጭ እያሳየች ትገኛለች። በተለይም ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ የኮሪደር ልማት ሥራዎች እንዲሁም እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ሀገራዊ ሜጋ ፕሮጀክቶች ስኬት ኢትዮጵያ ወደ አዲስ የብልጽግና ምዕራፍ እየተሸጋገረች መሆኗን የሚያረጋግጡ ማሳያዎች ናቸው።
በዚህ ሁለንተናዊ የለውጥ ማዕቀፍ ውስጥ፣ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በቂ አቅም፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና የተቀናጀ የመረጃ ሥርዓት ሳይገነባለት የቆየው የማዕድን ዘርፍ ዛሬ ላይ የዚህ የማንሠራራት ጉዞ ቁልፍ አካል ሆኗል።
በአዲሱ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ውስጥ ማዕድን ከግብርና፣ አምራች ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝም እና ቴክኖሎጂ ጋር በመሆን ከአምስቱ ዋና ዋና የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ ሆኖ ተለይቷል።
ይህ ስትራቴጂካዊ ውሳኔ ዘርፉን ከጥሬ ሀብት አቅራቢነት ወደ ጠንካራ የኢኮኖሚ ሞተርነት እያሸጋገረው ይገኛል። በተለይም በውጭ ምንዛሪ ግኝት ረገድ እየታየ ያለው ታሪካዊ እመርታ የዚሁ ሪፎርም ትሩፋት ነው።
የ2018 በጀት ዓመት ብቻ ኩባንያዎች እና ባህላዊ የወርቅ አምራቾች ከ44 ቶን በላይ የወርቅ ምርት በማምረት ወደ ገበያ በማቅረብ 5.7 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ገቢ ተገኝቷል።
ይህ ስኬት መንግሥት የወሰደው የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ሕገ-ወጥ የኮንትሮባንድ ዝውውርን በመግታት እና ባህላዊ አምራቾችን ወደ ህጋዊ የባንክ ሥርዓት በማስገባት ያመጣው ተጨባጭ ውጤት ነው።
ይህ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ግኝት የብሔራዊ ባንክን ክምችት ከማሳደግ ባለፈ፣ የጥቁር ገበያን ጫና በማቃለል እና የኢትዮጵያን የብድር አስተማማኝነት በማሻሻል አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ደግፏል።
በተጨማሪም ሌሎች አምራች ዘርፎች የካፒታል ዕቃዎችን ከውጭ ለማስገባት የሚፈልጉትን የፋይናንስ አቅም በመፍጠር ረገድ የማይተካ ሚና እየተጫወተ ነው።
ከውጭ ምንዛሪ ግኝት በተጓዳኝ፣ ዘርፉ በተኪ ምርቶች አቅርቦት እና በእሴት ጭመራ እያስመዘገበ ያለው ለውጥ ሌላው የሪፎርሙ ትልቅ ስኬት ነው።
ኢትዮጵያ የማዕድን ሀብቷን በጥሬው ወደ ውጭ ከሚላክበት አሠራር በማላቀቅ የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችን በግብዓት ለማስተሳሰር ሰፊ እንቅስቃሴ ጀምራለች።
ለዚህም የወርቅ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች፣ የሴራሚክ እና የሲሚንቶ ፋብሪካዎች፣ የተፈጥሮ ጋዝ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ እና የማዳበሪያ ፋብሪካ የመሠረተ ድንጋይ ተቀምጦላቸው ግንባታቸው እየተፋጠነ ይገኛል።
እነዚህ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የማዕድን ሀብትን እሴት ወደተጨመረበት ምርት በመቀየር፣ በውጭ ምንዛሪ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት፣ ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እና የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለማጠናከር የላቀ ፋይዳ አላቸው።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: