Search

ከቫቲካን እና ሞናኮ የሚልቀው የአፍሪካ የሰማይ በር

ሰኞ ጳጉሜን 02, 2018 151

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ በይፋ የተመረቀበት ታሪካዊ ዕለት፣ ለኪነ ሕንፃ እና ምሕንድስና ድል ብቻ ሳይሆን ለአዲስ አኅጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የሥልጣኔ ምዕራፍ መነሻ ነው። በዚሁ ዕለት ኢትዮጵያ ሌላ አዲስ ታሪክ ለመጻፍ ግብ አስቀምጣ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ይፋ ካደረጓቸው እና አጠቃላይ ወጪያቸው 30 ቢሊዮን አሜሪካ ዶላር በላይ ከሚገመተው ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል፣ 12.5 ቢሊዮን ዶላር በጀት የሚገነባው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።

ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነው የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ያለበት መልክዓ ምድራዊ ገደብ ነው።

ቦሌ ከባሕር ወለል በላይ 2 ሺህ 334 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኝ በመሆኑ፣ በአየር እፍግታ ማነስ ምክንያት አውሮፕላኖች ረጅም ርቀት በሚበርሩበት ወቅት የመጫን አቅማቸውን ወይም የነዳጅ መጠናቸውን እንዲቀንሱ ያስገድዳቸዋል።

በአንጻሩ በቢሾፍቱ የሚገነባው አዲሱ ማረፊያ ከቦሌ 400 ሜትር ያህል ዝቅ ብሎ መሠራቱ እጅግ ከፍተኛ የኦፐሬሽን ብልጫ ይፈጥራል። ይህ የተሻለ የአየር እፍግታ አውሮፕላኖች ሙሉ የመጫን አቅማቸውን ተጠቅመው ያለ ነዳጅ እና ጭነት ገደብ ወደ ሰሜን አሜሪካ፣ አውስትራሊያ እና ምሥራቅ እስያ ቀጥታ አኅጉር ተሻጋሪ በረራዎችን እንዲያደርጉ ያስችላቸዋል።

የአዲሱን አውሮፕላን ማረፊያ ግዙፍነት በተጨባጭ ሥዕል ለመረዳት የሚያርፍበትን 40 ካሬ ኪሎሜትር የቦታ ስፋት ከታወቁ ሉዓላዊ ግዛቶች ጋር ማነጻጸር በቂ ነው። ፕሮጀክቱ ያረፈበት ቦታ የቫቲካን ሲቲን አጠቃላይ ስፋት 81 እጥፍ፣ የሞናኮን 20 እጥፍ፣ እንዲሁም የማልዲቭስ ዋና ከተማ ማሌን ወደ 5 እጥፍ ገደማ የሚበልጥ ነው።

ከዚህም ባለፈ ከሳን ማሪኖ አጠቃላይ የመሬት ስፋት ውስጥ 65 በመቶውን የሚሸፍን አስገራሚ ግዝፈት አለው። ይበልጥ አድናቆትን የሚጭረው ደግሞ 660 ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት ያለው የመጀመርያው ምዕራፍ የተርሚናል ሕንፃ ብቻውን መላዋን የቫቲካን ግዛት አቅፎ 0.17 ካሬ ኪሎሜትር ትርፍ ቦታ ማስቀረቱ ነው።

በአጠቃላይ 30 ኪሎሜትር በሚረዝመው የአውሮፕላን ማረፊያው ኮሪደር ላይ አንድ ሰው በእግሩ ለመጓዝ ቢነሳ ያለ ዕረፍት 6 ሰዓት በላይ የሚጠይቅ በመሆኑ ፕሮጀክቱ ዘመናዊ አውቶማቲክ የተሳፋሪ ማጓጓዣ እና የውስጥ የኤሌክትሪክ ባቡር ትራንስፖርት ሥርዓትን በውስጡ አቅፏል።

በሁለት ምዕራፎች ተከፋፍሎ የሚገነባው እና የመጀመሪያ ምዕራፉ .. 2030 የሚጠናቀቀው ይህ ማረፊያ በሙሉ አቅሙ ሲጠናቀቅ በዓመት 110 ሚሊዮን ተሳፋሪዎችን እና 4 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ካርጎ ያስተናግዳል።

የሕንፃው ንድፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚታወቁት ዛሃ ሀዲድ አርክቴክቶች እና ዳር አል-ሃንዳሳህ ጥምረት የተዘጋጀ ሲሆን፣ ዲዛይኑ የምሥራቅ አፍሪካን ስምጥ ሸለቆ ተፈጥሯዊ ቅርጽ የተከተለ እና ሀገር በቀል የብዝኃ-ሕይወት ዕፅዋትን ያካተተ ክፍት የተፈጥሮ አየር የሚተነፍስበት የአትክልት ስፍራን ይዟል።

በተጨማሪም LEED Gold የአካባቢ ጥበቃ ደረጃን በሚያሟላ መልኩ የሙቀት መጠንን የሚቆጣጠር እና የዝናብ ውኃን መልሶ ለፍጆታ የሚያውል አረንጓዴ ቴክኖሎጂን የተላበሰ ነው። የትራንዚት መንገደኞችን ምቾት ለመጠበቅም 350 ክፍሎች ያሉት ዘመናዊ ሆቴል፣ የሲኒማ እና የንግድ ዞኖችን በማካተት የዓለም አቀፍ መስተንግዶ ጥበብን ያሳያል።

የግንባታው ፋይናንስ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ቀጥተኛ የዕዳ ጫና በማይፈጥር የተቀናጀ ልዩ ዓላማ ኩባንያ (SPC) ሞዴል ይመራል። 70 በመቶ ከብድር እና 30 በመቶ ከካፒታል በሚሸፈነው በዚህ ፕሮጀክት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ 700 ሚሊዮን ዶላር የመጀመሪያ ደረጃ ካፒታል ገቢ አድርጓል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ 500 ሚሊዮን ዶላር ቀጥታ ብድር የፈቀደ ሲሆን፣ ቀሪው ፋይናንስ ከዓለም አቀፍ ተቋማት የሚሰበሰብ ይሆናል።

ማኅበራዊ ኃላፊነትን በተመለከተም በቦታው የነበሩ 2 ሺህ 500 በላይ አባወራዎች መልሰው እንዲቋቋሙ መደረጋቸው ፕሮጀክቶች የአካባቢን ነዋሪ የሚያፈናቅሉበትን ታሪክ የሻረ ነው።

ይህ ትውልድ ተሻጋሪ ፕሮጀክት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያነገበውን "ራዕይ 2035" ስትራቴጂ ለማሳካት እና በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ማዕቀፍ የአኅጉሪቱ ዋነኛ የካርጎ እና ሎጂስቲክስ በር ለመሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

ግዙፍነቱ፣ ዘመናዊነቱ እና ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታው ኢትዮጵያን የዓለም አቀፍ ትራንዚት፣ የንግድ እና የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ሥፍራዋን በማረጋገጥ አዲሱን የአቪዬሽን ምዕራፍ በደማቁ ይጽፋል።

በለሚ ታደሰ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: