የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት (Ethiopian Labor Market Information System - ELMIS) ፕሮጀክት ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል በመፈጸም የተጠረጠረውን የኢትዮጵያ ሥራ ገበያ መረጃ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ የነበረው አቶ ብርሃኑ አለቃ አስገዶም እና በግብረ አበሮቹ ላይ ከሐምሌ 17 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ሲያካሂድ የቆየውን ጥልቅ ምርመራ በማጠናቀቅ ለፍትሕ ሚኒስቴር ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ልኮ ክስ መመስረቱን አስታውቋል።
ብርሃኑ አለቃ አስገዶም እና ሌሎች የተቋሙ ሠራተኞች፣ የሠራተኛና አሠሪ አገናኝ ኤጀንሲ ባለቤቶች እና ሌሎች ግለሰቦችን ጨምሮ 13 ሰዎች በዚህ ወንጀል ውስጥ የተሳተፉ ሲሆን፤ ተጠርጣሪዎቹ የተሰጣቸውን የመንግሥት ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው እና ፕሮጀክቱን ከአሠራር ውጭ በማንቀሳቀስ ከጅምሩ የሲስተሙ የጥራት ደረጃ በተገቢው ሳይረጋገጥ ሥራ እንዲጀምር ማድረጋቸውን ፖሊስ በምርመራው አረጋግጧል።
ብርሃኑ አለቃ አስገዶም ላልተማሩ ወይም በቂ ሥልጠና ላልወሰዱ ለ81,236 ግለሰቦች ሕገ ወጥ የሙያ ብቃት ምዘና ሰርተፊኬት (COC) በሲስተም እንዲሰጣቸው ያስደረገ ሲሆን፤ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሠራተኛ ላልሆኑና ተቋሙ ከማያውቃቸው ሦስት ግለሰቦች ጋር በመመሳጠር ልዩ የሲስተም አስተዳዳሪ (Admin) መብት በመስጠት ዜጎች ያልሠለጠኑበትን ሐሰተኛ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ እንዲያገኙ ማድረጉ በምርመራ ተደርሶበታል።
ለዚህ የወንጀል ድርጊት ሁለት ሐሰተኛ የባንክ ሒሳብ ደብተሮች እንዲከፈቱ በማድረግ በዚህ ሕገ ወጥ መንገድ አጠቃላይ 1 ቢሊዮን 13 ሚሊዮን 609 ሺህ 241 ብር ከ93 ሣንቲም መሰብሰቡ በምርመራ ተረጋግጧል።
በተጨማሪም የወንጀሉ ፍሬ የሆነ በባንክ ሒሳብ ውስጥ ይገኝ የነበረ 249 ሚሊዮን ብር የታገደ ሲሆን፤ ወንጀለኞቹ በረቀቀ ዘዴ ገንዘቡን ወደ ክሪፕቶከረንሲ (Cryptocurrency) በመቀየር ያስቀመጡትን 965 ሺህ 508 ዶላር ከፍተኛ ጥበብ በተሞላበትና በቴክኖሎጂ በታገዘ ምርመራ በፍርድ ቤት በማሳገድ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲገባ ተደርጓል።
ከዚህ በተጨማሪም ተጠርጣሪዎቹ የውጭ ምንዛሪ ሳያስገቡ የታገዱ ኤጀንሲዎችን እግድ ያለአግባብ በማንሳት 10 ሚሊዮን 100 ሺህ ብር ጉቦ የተቀበሉ እና 64,500 ዜጎችን በሐሰተኛ ቪዛ ሰነድ ወደ ጆርዳን እና ወደ ሌሎች የዓረብ ሀገራት በመላክ ለከፍተኛ እንግልት መዳረጋቸውን ፖሊስ ባደረገው የተጠናከረ ምርመራ ማረጋገጥ ችሏል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር (INSA)፣ ከፋይናንስ ደኅንነት መረጃ ማዕከል እና ከብሔራዊ ባንክ ጋር በመቀናጀት ባካሄደው ምርመራ በተጠርጣሪው ስም በለሚ ኩራ፣ በቦሌ እና በቂርቆስ ክፍለ ከተሞች የተገዙ ከ55 ሚሊዮን እስከ 68 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ 6 ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች እንዲሁም በ68 ሚሊዮን ብር የተገዛ አንድ V6 ዘመናዊ መኪና በኤግዚቢትነት በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ አድርጓል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በዚህ ወንጀል ውስጥ የተሳተፉ እና ሕጋዊነትን ሽፋን በማድረግ መንግሥት ማግኘት የነበረበትን የውጭ ምንዛሪ ሳያስገቡ በቀሩ ኤጀንሲዎች ላይ እያደረገ ያለውን ምርመራ አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጿል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ልጆቻቸው ወደ ውጭ ሀገር ሄደው መዳረሻቸው የጠፋባቸው ቤተሰቦች እና ከዚህ ወንጀል ጋር በተያያዘ መረጃ ያላቸው ዜጎችም በዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ (EFPApp)፣ በነፃ የስልክ መስመር (991) እና በሰው አልባ ስማርት ፖሊስ ጣቢያ (SPS) አማካኝነት ጥቆማ እንዲሁም በወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ በአካል በመቅረብ ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ ጥሪ ያቀርባል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: