የኢትዮጵያ ታሪክ በነፃነት፣ በጀግንነት እና በየትውልዱ መሥዋዕትነት የተጻፈ ታሪክ ነው። ይህን የነፃነት ታሪክ ከትውልድ ትውልድ በኩራት እንድናስቀጥል ካደረጉን ታላላቅ ተቋማት መካከል ደግሞ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ ሚና አለው።
ሠራዊታችን የሀገር ሉዓላዊነት፣ የሕዝብ ደኅንነት እና የብሔራዊ ክብር ዘብ ነው። ዛሬም ኢትዮጵያ በደኅንነት ፈተናዎች እና በቀጣናዊ ውጥረቶች መካከል ባለችበት ወቅት መከላከያ ሠራዊታችን የሀገርን ድንበር፣ የሕዝብን ደኅንነት እና ሉዓላዊነትን የመጠበቅ ሕገ መንግሥታዊ ተልዕኮውን በብቃት በመወጣት ላይ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ስለ ኢትዮጵያ ወታደር ወኔ እና ጀግንነት ሲያነሡ፣ የሠራዊቱን ጽናት፣ መሥዋዕትነት እና ለሀገር ያለውን ቁርጠኝነት አጽንዖት ሰጥተው ይገልጻሉ።
ይህም የሚያስታውሰን እውነት አለ፤ የኢትዮጵያ ወታደ እር ጥንካሬ በውጊያ ሜዳ ብቻ ሳይሆን፣ በተልዕኮው ላይ ባለው ታማኝነት እና በሕዝቡ ደኅንነት ላይ ባለው ኃላፊነትም ይገለጻል።
የሌሎች ወገኖች ምስክርነትም የዚህን ተልዕኮ ዋጋ ያሳያል። የአፍሪካ ኅብረት እ.አ.አ በ2024 በአዲስ አበባ በተካሄደው የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ጉባኤ ላይ፣ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ እና ለዓለም ሰላም የምታበረክተውን አስተዋፅኦ አድንቋል።
የኢትዮጵያ ወታደሮች በዓለም አቀፍ እና በአፍሪካ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ያከናወኑት ሥራ ለዚህ ምስክር ነው።
የሠራዊታችን ትልቁ ኃይል የሕዝብ ድጋፍ ነው። ሕዝቡ በሞራል እና በማኅበራዊ አጋርነት ከሠራዊቱ ጎን መቆሙ የጽናቱን መሠረት ያጠናክራል። ይህ ድጋፍ ለሀገር ሰላም፣ ለዜጎች ደኅንነት እና ለሠራዊቱ ሙያዊ ብቃት የሚቆም አጋርነት ነው።
ኢትዮጵያ በመከላከያ ሠራዊቷ ክንድ ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ ቆማለች፤ ወደፊትም ጠንካራ ሠራዊት፣ የተባበረ ሕዝብ እና የሰላም ፍላጎት ተደምረው ሲጓዙ #የትልቋሀገራችን ሉዓላዊነት እና ክብር ይበልጥ ይጸናሉ።
በዮናስ በድሉ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: