የአንድ ሀገር ዘመናዊነት እና ብልፅግና የሚለካው ሕዝቦቿ መሠረታዊ እና አስተዳደራዊ አገልግሎቶችን በሚያገኙበት ፍጥነት፣ ምቾት እና ጥራት ነው።
ለዘመናት የቆየው እና ዜጎችን ከአንድ መሥሪያ ቤት ወደ ሌላ መሥሪያ ቤት ያንከራትት የነበረው አሠራር፣ የዜጎችን ጊዜ እና እንግልት ከመጨመሩ ባሻገር ለብልሹ አሠራር በር ሲከፍት ቆይቷል።
ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ይህንን የቢሮክራሲ ሂደት በማስወገድ፣ አገልግሎቶችን ወደ አንድ ማዕከል ያመጣውን "መሶብ" የተሰኘውን ዘመናዊ አሠራር በመተግበር ላይ ትገኛለች።
መሶብ የተበታተኑ እና የተለያዩ የመንግሥት እና የማኅበራዊ አገልግሎቶችን በአንድ ጥላ ሥር በማስተባበር ለዜጎች ፈጣን እና ምቹ አሠራርን የዘረጋ አዲስ ምዕራፍ ነው።
ዜጎች ቀደም ሲል ለተለያዩ ጉዳዮች በርካታ መሥሪያ ቤቶችን ለማዳረስ ያባክኑት የነበረውን ጉልበት፣ ጊዜ እና ገንዘብ በአንድ ማዕከል እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። ይህም በቢሮክራሲ የተወጠረውን የአገልግሎት አሰጣጥ ከሥሩ በመቀየር የአገልግሎት ፈላጊውን ተጠቃሚነት እና እርካታ የሚያረጋግጥ ነው።
የአገልግሎት አሰጣጥን ወደ አንድ ማዕከል ማምጣት የጊዜ ቁጠባ ብቻ ሳይሆን መልካም አስተዳደርን የማስፈን ትልቅ መሣሪያ ነው። መሶብ የሰዎችን እና የመሥሪያ ቤቶችን ቀጥታ ግንኙነት በመቀነስ፣ አሠራሮችን ግልጽ እና ተጠያቂነት ያላቸው በማድረግ ለሙስና በር የሚከፍቱ ክፍተቶችን ይዘጋል።
በዲጂታል እና በዘመናዊ አሠራር የተደገፈው ይህ ማዕከል እያንዳንዱ ዜጋ ያለ እንግልት እና ያለ አድልዎ እኩል፣ ፈጣን እና ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኝ ያደርጋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመደመር መንግሥት ምሥረታ ላይ፦ “ለአዲሱ ዘመን ንቁ እና ብቁ ለማድረግ የጀመርናቸው የዲጂታል ኢትዮጵያ ጉዞዎች፣ ሀገራችን የአዲሱን ዓለም ጎርፍ ዋኝታ እንድትሻገር ብቻ አላስቻሏትም። በአንፃሩ የመዋኛውንም ሁኔታ እንድትወስን ዐቅም እየፈጠሩላት ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትም የዚህ ሀገራዊ ዕይታ እና የዲጂታል ኢትዮጵያ ጉዞ አካል በመሆን፣ ኢትዮጵያ የራሷን የአገልግሎት አሰጣጥ ፍጥነት እና ጥራት በራሷ አቅም እንድትወስን የሚያስችላትን መዋቅራዊ አቅም እየፈጠረ ይገኛል።
የመሶብ አገልግሎት መስፋፋት የዜጎችን የዕለት ተዕለት እንግልት በመቀነስ፣ በሥራ እና በምርታማነት ላይ የሚያወጡትን ጊዜ በማሳደግ ረገድ የጎላ ድርሻ አለው።
ይህ አሠራር ለሀገር ውስጥ ዜጎች ብቻ ሳይሆን ለኢንቨስትመንት እና ለንግድ እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር የሀገራችንን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያፋጥን እና የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ በተግባር የሚያረጋግጥ ሂደት ነው።
በሔዋን ጌታቸው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: