በአሁኑ የዓለም አቀፍ አሰራር ሥርዓት ውስጥ የሳይበር ምህዳር ከላቀ የኢኮኖሚ ትስስር ባሻገር የሀገራት የጂኦፖለቲካዊ ሽኩቻና የስትራቴጂካዊ የበላይነት መፋለሚያ መድረክ ሆኗል።
ቀደም ሲል ለፈጠራና ለመረጃ ልውውጥ የሚያገለግል ገለልተኛ የዲጂታል መሰረተ ልማት ተደርጎ ይወሰድ የነበረው የሳይበር ዓለም፣ አሁን ላይ ከሀገራት የሀይል አሰላለፍ፣ ብሔራዊ ሉዓላዊነትና ከከፋ ቀጠናዊ ስጋት ጋር በጥብቅ የተያያዘ ምዕራፍ ላይ ይገኛል።
በተለይም በብሪክስ ውስጥ የዲጂታል ትብብር፣ የሳይበር ደህንነት፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎት አስተማማኝነት እና የህዝባዊ አመኔታ ግንባታ ላይ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ለደቡበ ዓለም ሀገራት አዲስ ስትራቴጂካዊ አቅጣጫ በመፍጠር ላይ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ ይህንን ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ነባራዊ ሁኔታ በመገንዘብ፣ የዲጂታል ምህዳሯን ከሳይበር ስጋቶች መጠበቅ የሀገራችንን የዲጂታል ሉዓላዊነት፣ የዜጎችን ደህንነትና አጠቃላይ የልማት ጉዞን የማስጠበቅ ወሳኝ ጉዳይ አድርጋ በመንቀሳቀስ ላይ ትገኛለች።
በዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ የተመዘገቡት የኢንተርኔት ተጠቃሚነት መስፋፋት፣ የቴሌኮም ዘርፉ ለውድድር መከፈት፣ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቶች ማደግና የመንግሥት አገልግሎቶችን በዲጂታል መንገድ የማቅረብ እርምጃዎች ለትራንስፎርሜሽኑ ጠንካራ መሠረት ጥለዋል።
ይህንን ስኬት ወደ ላቀ ምዕራፍ በማሸጋገር የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ራዕይን እውን ለማድረግና የቴክኖሎጂ እድገትን የሀገራዊ ብልጽግና አቅም ለማድረግ በስፋት እየተሰራ ይገኛል።
ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ቴክኖሎጂ የምርምርና ልማት ዘርፍ ላይ የሰጠችው ልዩ ትኩረት እና ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች ለሌሎች አፍሪካውያን ሀገራት ትልቅ አርዓያነት ያለው ተግባር ሆኖ ተመዝግቧል።
በአገልግሎት፣ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት እና በሌሎች ወሳኝ ዘርፎች የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን በመጠቀም የምታከናውነው ተግባር፣ በብሪክስ ውስጥ ያላትን የቴክኖሎጂ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ያሳደገው ከመሆኑም በላይ ከአፍሪካና ከደቡበ ዓለም ሀገራት ጋር የሚደረጉ የደቡብ-ደቡብ ትብብሮችን እንደ አዲስ እንዲያሰራጩ መንገድ ከፍቷል።
ይህ የኢትዮጵያ የዲጂታል ምህዳር መጠናከር፣ የሳይበር ደህንነት ጥበቃ እና የሰው ሰራሽ አስተውሎት ምጥቀት ሀገራችን በዲጂታል ሉዓላዊነቷ የጸናች #ትልቅሀገር፣ በቴክኖሎጂና በፈጠራ የተራመደ #ትልቅሕዝብ እንዲሁም ለአፍሪካ የዲጂታል ዕድገት የፊት አውራሪነትን የሚመራ #ታላቅርዕይ ያላት መሆኗን በተግባር ያረጋገጠ ታሪካዊ ምዕራፍ ነው።
በሰለሞን ገዳ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: