የትግራይ ክልል የፌዴራል መንግሥት ባለአደራ አስተዳደር የሕዝብ አገልግሎቶችን ሙሉ በሙሉ ለማስጀመር ሰፊ ዝግጅት አጠናቋል ሲሉ የትግራይ ክልል የፌዴራል መንግሥት ባለአደራ አስተዳደር የአስተዳደር እና የሕዝብ አገልግሎት ዋና አስፈጻሚ አቶ አሰፋ አብርሃ ገለጹ።
በክልሉ ዘላቂ ሰላም በማስፈን የሕዝብ አገልግሎቶችን ሙሉ በሙሉ ለማስጀመር እና የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ የማስፈታት፣ ከወታደራዊ መዋቅር የማሰናበት እና ወደ መደበኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ህይወት መልሶ የማዋሃድ ሂደቱን የሚያጠቃልለውን የዲዲአር ፕሮግራም በተሳካ ሁኔታ ለማስፈጸም ሰፊ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
አቶ አሰፋ ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የትምህርት፣ የጤና፣ የእርሻ እና የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎቶችን ቅድሚያ በመስጠት መልሶ ለማስጀመር በርካታ ዝግጅቶች ተጠናቀው ወደ ተግባር መገባቱን አብራርተዋል።
በመቐለ ከተማ እና በሌሎች ወረዳዎች የወረዳ፣ የጣቢያ እና የቀበሌ አስተዳደሮችን በሕዝብ መራጭነት የማቋቋም ሥራ እየተጠናቀቀ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
የአስተዳደር ኮሚቴዎች ከተደራጁ በኋላ የአካባቢውን ሰላም የሚያስጠብቁ የፖሊስ እና ሚሊሻ የጸጥታ ኮሚቴዎች እንደሚቋቋሙ፣ በመቀጠልም የንግድ እና የማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ሙሉ በሙሉ እንደሚጀመሩ ተገልጿል።
በክልሉ ባጋጠመው ድርቅ እና መፈናቀል ምክንያት የሚገጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ ከመንግሥት፣ ከሀገር ውስጥ እና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለቀድሞ እና አዳዲስ ተፈናቃዮች የእርዳታ ማከፋፈል ሥርዓት እየተዘረጋ ስለመሆኑም ዋና አስፈጻሚው አያይዘው ገልጸዋል።
የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ መደበኛ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት ለመመለስ የሚደረገው የዲዲአር ፕሮግራም ከፍተኛ ውጤት እያሳየ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አሰፋ፣ በስታዲየም ከተካሄደውና በርካታ ወጣቶች ከተሳተፉበት ምዝገባ በተጨማሪ የሰዎች ፍሰት እና ጫና ለመቀነስ በሽሬ፣ አደሐሙስ፣ ማይጨው እና በሌሎች አካባቢዎች አዳዲስ የምዝገባ ማዕከላት መከፈታቸውን አስታውሰዋል።
"አብዛኛው ወጣት፣ ነጋዴ፣ አስተማሪ እና የመንግሥት ሰራተኛ የነበረው ኃይል ሰላምን መርጦ ወደ መደበኛ ሕይወቱ ለመመለስ ፍላጎት አሳይቷል፤ ከዚህ በኋላ ለጦርነት አማራጭ የለም፤ ሰላም ብቻ ነው የሚጠቅመው" ብለዋል አቶ አሰፋ።
አክለውም ህብረተሰቡ የሐሰት ፕሮፓጋንዳዎችን እና የስጋት ድምጾችን ወደ ጎን በመተው ወደ ሰላምና ልማት መመለሱን፣ ከዓመታት ጦርነት እና መከራ በኋላ አሁን በክልሉ አዲስ የተስፋና የሰላም አየር መንፈስ መጀመሩን አረጋግጠዋል።
#ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በሜሮን ንብረት
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: