Search

የጣና ፎረም ተሳታፊዎች ወደ ባሕር ዳር ከተማ እየገቡ ነው

ሓሙስ ጥቅምት 12, 2019 78

በነገው ዕለት በሚጀምረው 12ኛው የጣና ፎረም ላይ የሚሳተፉ እንግዶች ወደ ባሕር ዳር ከተማ በመግባት ላይ ይገኛሉ፡፡

በአፍሪካ ሰላም፣ ጸጥታ እና ደኅንነት ላይ ጥልቅ ምክክር የሚያደርገው 12ኛው የጣና ፎረም ከጥቅምት 13 እስከ 15 ቀን 2019 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ ይካሄዳል፡፡

ለጉባኤው ጥሪ የተደረገላቸው የአፍሪካ መሪዎች፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ ዲፕሎማቶች እና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ወደ ከተማዋ በመግባት ላይ ይገኛሉ።

በዚህም የሴራሊዮን የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኤርነስት ባይ ኮሮማ በፎረሙ ላይ ለመሳተፍ  ባሕር ዳር የገቡ ሲሆን በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱም፣ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር)፣ የባሕር ዳር ከተማ ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው እና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው እንደገለጹት፣ የጣና ፎረም ቀጣናዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የሰላምና ደኅንነት ጉዳዮች የሚነሱበት ታላቅ መድረክ ነው።

 

ፎረሙ ውጤታማ እንዲሆን ከአማራ ክልል ጋር በመናበብ በቂ ዝግጅት መደረጉን የጠቆሙት ቃል አቀባዩ፣ በኮሪደር ልማት ይበልጥ ያሸበረቀችው የባሕር ዳር ከተማ ማራኪ መልክዓ ምድርና ምቹ ከባቢ አየር ተሳታፊዎች በተረጋጋ መንፈስ እንዲመክሩ ከማስቻሉም በላይ የከተማዋን የቱሪዝም መዳረሻነት አጉልቶ እንደሚያሳይ ገልጸዋል።

 

 

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: