Search

ኢትዮጵያውያን በልግስና ከዓለም የ22 ኛ ደረጃን ይዘዋል - ቻሪቲ ኤድ ፋውንዴሽን

ረቡዕ ነሐሴ 14, 2017 102

ሰሞኑን ቻሪቲ ኤድ ፋውንዴሽን ይፋ ባደረገው ጥናት ከሀብታም ሀገራት ይልቅ የአፍሪካ አዳጊ አገራት ለጋስ እንደሆኑ አስታውቋል።

ከተመሰረተ የመቶ ዓመት እድሜ ያለው እና ዋና ፅህፈት ቤቱን በእንግሊዝ ለንደን ያደረገው ቻሪቲ ኤድ ፋውንዴሽን ይፋ ባደረገው ጥናት አፍሪካውያን ከገቢያቸው በአማካኝ 1.54 በመቶውን ለተለያዩ የበጎ አድራጎት ተግባራት ይለግሳሉ።

በአንጻሩ አውሮፓውያን ደግሞ ከገቢያቸው 0.64 በመቶውን ብቻ እንደሚለግሱ አስታውቋል።

በሀብታም ሀገራት የሚኖሩ ሰዎች ይበልጥ ለጋስ እንደሆኑ የሚታሰበው የተሳሳተ ስሌት መሆኑን ያስገነዘበው ጥናቱ በበለፀጉ ሀገራት ከሚኖሩ ሰዎች ይልቅ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ውስጥ የሚኖሩት ለልግስና እጃቸውን እንደሚፈታ አሳይቷል ።

በዚህም መሰረት ጠንካራ ኢኮኖሚ ያላቸው እንደ ጃፓን፣ ፈረንሳይ እና ጀርመን ያሉ ሀገራት ውስጥ ያሉ ሕዝቦች ለበጎ ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ ለእምነት ተቋማት እና ለመሰል ሰብዓዊ እርዳታ አገልግሎት የሚለግሱት ከገቢያቸው 0.16 በመቶ እና ከዚያ በታች እንደሆነ ጥናቱ አመላክቷል።  

በተቃራኒው የአፍሪካ ሀገራት ከላይ ለተጠቀሱት በጎ ተግባራት፡ ከሚያገኙት ዝቅተኛ ገቢ ላይ 1.54 በመቶውን ይለግሳሉ ተብሏል ።

እ.አ.አ. ከ2009 ጀምሮ ይህን መሰል የጥናት ውጤቶችን በየዓመቱ ይፋ የሚያደርገው ቻሪቲ ኤድ በዘንድሮው ዓመት ጥናቱ አፍሪካን በአለም ለጋስ ከሆኑ አህጉራት መካከል በአንደኛነት አስቀምጧታል።

ከሀገራት መካከል ደግሞ ኢትዮጵያውያን ከሚያገኙት ገቢ ላይ 1.51 በመቶውን ለቀጥታ እርዳታ፣ ለበጎ አድራጎት ተቋማት እና ለሐይማኖታዊ ተቋማት በመለገስ በዓለም ካሉ ሀገራት የ22ኛ ደረጃን እንደያዙ ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል።

ቻሪቲ ኤድ ፋውንዴሽን ባወጣው ሪፖርት መሰረት የስሎቫንያ ነዋሪዎች ከገቢያቸው ላይ 0.16 በመቶውን በመለገስ በዓለም የመጨረሻውን ደረጃ ይዘዋል።

 

በዋሲሁን ተስፋዬ