ኢትዮጵያውያን በረጅም የታሪክ ጉዟቸው ውስጥ በልዩነቶች እና በውስጥ ውጣ ውረዶች ውስጥ ባለፉባቸው አጋጣሚዎች እንኳ ሳይቀር፣ የሀገር ህልውና እና ደኅንነት አደጋ ላይ ሲወድቅ በአንድነት የመቆም የጸና ባህል አላቸው።
ከ130 ዓመታት በፊት በታላቁ የዓድዋ ድል የተመሰከረው ይህ የማይበገር የአብሮነት መንፈስ፣ የውጭ ወራሪዎችን አሳፍሮ ከመመለሱ ባሻገር ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች ሁሉ የነጻነት እና የልዕልና ተምሳሌት ሆኖ በወርቅ ብዕር ተጽፏል።
ይሁን እንጂ ከዓድዋ የድል ማግስት ጀምሮ የኢትዮጵያን የዕድገት ጉዞ ሲፈታተን እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ስሟን በታሪክ ጥላሸት ሲቀባ የኖረው ሌላኛው ታሪካዊ ጠላት ድህነት ነበር።
ከአያቶች የተወረሰው የአልበገር ባይነት፣ የመተባበር እና የጋራ ቁርጠኝነት መንፈስ በትውልዱ ውስጥ ህያው ሆኖ መኖሩን ዳግማዊ ዓድዋ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለዓለም አስመስክሯል።
ጳጉሜ 4 ቀን 2017 ዓ.ም ግድቡ ሙሉ በሙሉ ተመርቆ ወደ ሥራ መግባቱ እና ሙሉ በሙሉ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ የተበሰረበት ታሪካዊ ዕለት የዚሁ ታላቅ ድል ህያው ማረጋገጫ ነው።
ይህ ታሪካዊ ክስተት "አብሮነት ለሀገራዊ ጽናት - በልዩነት ውስጥ ያለ ውበት" በሚል መሪ ሐሳብ ከሚከበረው የጳጉሜ 4 የ"ኅብር ቀን" ትርጉም ጋር በቀጥታ የተቆራኘ ነው።
የኢትዮጵያውያን ብዝኃነት የስጋት ምንጭ ሳይሆን የሀገር ግንባታ ዋና አቅም እና ውበት መሆኑን የግድቡ ግንባታ በግልጽ አሳይቷል።
ዜጎች በፖለቲካ፣ በብሔር እና በእምነት ያላቸውን ልዩነቶች እንደ ሀገራዊ ጌጥ በመውሰድ፣ በአንድ ዓላማ ስር ተሰልፈው ታሪካዊ ጠላታቸውን ድህነትን ለመዋጋት ቆርጠው ተነስተዋል።
ያለ ውጭ እርዳታ እና ብድር፣ በኢትዮጵያውያን ላብ፣ ዕውቀት እና ገንዘብ ተገንብቶ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ የገባው ይህ ሜጋ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ ከተረጂነት አዙሪት በገዛ እጇ መውጣት እንደምትችል አረጋግጧል።
የግድቡ መጠናቀቅ ለሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች እና ለዜጎች በቂ ኤሌክትሪክ ከማቅረቡ ባሻገር እንደ ኬንያ፣ ጅቡቲ እና ሱዳን ላሉ ጎረቤት ሀገራት ኃይል በመሸጥ የቀጣናውን የኢኮኖሚ ትስስር የሚያጠናክር እና የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝ የልማት ዋልታ ሆኗል።
ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ስኬት ኢትዮጵያ በገዛ ወንዟ ላይ የነበራትን ሕጋዊ እና ተፈጥሯዊ መብት በተግባር ያስከበረችበት አዲስ የሉዓላዊነት ምዕራፍ ነው።
አያቶች በጠመንጃ እና በደማቸው ዓድዋ ላይ የሀገርን ዳርቻ ያስከበሩትን ያህል፣ የዚህ ዘመን ኢትዮጵያውያንም በሙያቸው፣ በገንዘባቸው እና በላባቸው ዳግማዊ ዓድዋ የሆነውን የሕዳሴ ግድብ እውን በማድረግ ድህነትን እያከሸፉ ነው፤ የብዝኃነትን ውበትንም በልማት እያጸኑ ነው።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: