ጳጉሜን ወር ስንቀበል በከፍተኛ ድምቀት ከምናከብራቸው ዕሴቶች አንዱ "የኅብር ቀን" ነው።
የኅብርን፣ የትብብርን እና የአንድነትን ትርጉም በተግባር ማየት ከፈለግን፣ ዓይኖቻችንን ወደ አዲስ አበባ ከተማ የወንዞች ዳርቻ እና የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች መመለስ በቂ ነው።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተከናወኑት እነዚህ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ከተማዋን ውበት ከማልበስ ባለፈ የነዋሪዎቿን የደኅንነት፣ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ሕይወት ሙሉ በሙሉ የቀየሩ፣ የኅብራችን ማሳያዎች ናቸው።
የአዲስ አበባን የትናንት ገጽታ ስንቃኝ፣ ወንዞቻችን ኬሚካሎች እና ቆሻሻዎች የሚጣሉባቸው፣ በክረምት ለጎርፍ አደጋ የሚያጋልጡ እና ለከባድ ጠረን የተጋለጡ የከተማዋ ህመሞች ነበሩ።
ዛሬ ግን ይህ ግዙፍ መሠረተ ልማት የወንዞችን የተፈጥሮ ማንነት ከመገንባት ጀምሮ፣ ሥፍራዎቹን ወደ ንጹሕ፣ ጤናማ እና እፎይታን ወደሚሰጡ አረንጓዴ የሕዝብ መናፈሻዎች ቀይሯቸዋል።
እነዚህ የልማት ሥራዎች የአካባቢ ሥነ-ምህዳርን ከመጠበቅ ባሻገር፣ የሕብረተሰቡን የኑሮ ዘይቤ ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረ የትውልድ ታላቅ ዐሻራ ሆኗል።
ለዚህ አስደናቂ የከተማዋ ትራንስፎርሜሽን ትልቁ ማሳያ ከእንጦጦ ተራራ ስር ተነስቶ እስከ ቀበና ድልድይ የተዘረጋው የልማት ፕሮጀክት ነው።
በአጠቃላይ ሰፊ ቦታን የሸፈነው ይህ ፕሮጀክት ተፈጥሮን ከዘመናዊ መሠረተ ልማት ጋር በልዩ ጥበብ ያስተሳሰረ ነው።
ለተፋሰስ ጥበቃ እና ለውኃ መጠን መጨመር የባሕር ዛፎች ተመንጥረው በሀገር በቀል እፅዋት መተካታቸው እንዲሁም የእርከን እና የጎርፍ መከላከያ ግንባታዎች የአፈር መሸርሸርን ሙሉ በሙሉ አስቁመዋል።
በዚህም ምክንያት ትናንት በቆሻሻ የተሞላው ወንዝ ዛሬ ኩልል ባለ ውኃ መፍሰስ ጀምሯል፤ አካባቢውም ለብዝኃ ሕይወት መመለሻ እና ለሰላም ቀጠናነት በቅቷል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ ፕሮጀክቱ ነዋሪዎችን በማስተሳሰር ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
በወንዙ ዳርቻ የተገነቡት የእግረኛ መንገዶች፣ ማዶ እና ማዶን የሚያገናኙት ተንጠልጣይ ድልድዮች፣ ከእንጦጦ ጀምሮ የተዘረጋው የሃይኪንግ መንገድ፣ የመንገድ መብራቶች፣ ቤተ መጽሐፍት፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ ካፌቴሪያዎች እና የልጆች መጫወቻዎች የከተማዋን ኅብርና ትስስር ከማሳለጥ ባለፈ የቱሪስት መስህብ በመሆን ነዋሪው ያለ ስጋት እንዲገናኝና እንዲዝናና ምቹ ሁኔታ ፈጥረዋል።
የኅብር ቀን ስኬት የሚለካው በሁለንተናዊ እድገት በመሆኑ የዚህ ፕሮጀክት ሌላው ትልቅ ስኬት የከተማ ግብርናን፣ የምግብ ዋስትናንና የኢኮኖሚ እድሎችን አቀናጅቶ የያዘ መሆኑ ነው።
በልማቱ የተተከሉ በርካታ ዛፎች ለውበት ብቻ ሳይሆን እንደ እንጆሪ፣ ማንጎ እና አፕል ያሉ የፍራፍሬ ምርቶች የሚገኙባቸው ናቸው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የተጀመረው ዘመናዊ የንብ ማነብ ስራ የወንዝ ዳርቻዎችን ለላቀ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ማዋል እንደሚቻል አሳይቷል። እንዲሁም የጽዳት ንቅናቄውን በዘመናዊ ዲጂታል አሰራር መምራት መጀመሩ የልማቱ የዘመናዊነት መገለጫ ነው።
ትናንት ከፍተኛ የደኅንነትና የጤና ስጋት የነበሩ ቦታዎች፣ ዛሬ በጋራ ራዕይ እና በኅብር ወደ ሕዝብ መጋቢነት፣ ወደ ሥራ እድል ፈጠራ እና ወደ አይን ማረፊያነት ተለውጠዋል።
ይህ ፈጣን እና ጥራት ያለው ኢንቨስትመንት አዲስ አበባን አረንጓዴ፣ በኢኮኖሚ ንቁ እና ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የተዋሃደች ዘመናዊ መዲና በማድረግ፣ የወደፊቷን ዕጣ ፈንታ በጽኑ መሠረት ላይ ገንብቷል።
የኅብር ቀንን ስናከብር፤ ሀሳብ እና ጉልበት ከተባበረ፣ ቆሻሻን ወደ ጸጋ፣ መለያየትን ወደ ድልድይ መቀየር እንደሚቻል እነዚህ የልማት ሥራዎች ምስክሮቻችን ናቸው።
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: