ለዘመናት ስሟ እንጂ ግብሯ እጅግ ያረጀ፣ ውበቷ በጊዜ እና በቸልተኝነት የረገፈ፣ ከራሷ ስያሜ ጋር ክፉኛ የተጣላች ከተማ ነበረች። ለዓመታት የተሸከመችው የድህነት፣ የብልሹ አሠራር እና የተበላሸ ፕላን ሸክም ጀርባዋን አጉብጦት ኖሯል። "አዲስ" የሚለው ቃል ከመቆርቆሯ ዘመን ጀምሮ በመዝገበ ቃላት እንጂ በመንገዶቿ ላይ ጎልቶ አይታይም ነበር።
ታላቋ የአፍሪካ መዲና፣ የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከል እየተባለች በታሪክ መድረክ ብትሞገስም፣ ወደ ጓዳዋ ስንገባ ግን ውስጧ የድህነት፣ የተስፋ መቁረጥ ማሳያ፣ የብክለት እና የጽዳት መጓደል ሙዚየም ሆና ቆይታለች።
ወደ ሰርጧ ጠለቅ ብለን ስንገባ የነበረው ምሥል እነዚያ ጠባብ፣ ትንፋሽ አጠር ሰርጦች፣ የፀሐይ ብርሃን ፈጽሞ የማያውቋቸው፣ ጨለማ እና እርጥበት ያረገዘባቸው መንደሮች የቅርብ ጊዜ ትዝታዎቻችን ናቸው።
ከሰዎቹ ፍቅር ይልቅ ቤቶቹ ክፉኛ የተፋቀሩ እና የተጠባበቁ እስኪመስሉ ድረስ፣ አንዱ አሮጌ ጎጆ በሌላው ትከሻ ላይ ተደግፎ እና ተጣብቆ የሚኖርባቸው ቀዬዎች ነበሩን።
በእነዚህ ሰርጦች ውስጥ አስክሬን በቃሬዛ በሰላም መውጣት የማይችልባቸው ጠባብ መግቢያዎች፣ ድንገት የእሳት አደጋ ቢነሣ የጎረቤት ዕጣ ፈንታ ተቃቅፎ አብሮ መቃጠል ብቻ የነበረባቸው፣ መውጫ እና መግቢያ ያጡ መንደሮች መዲናዋን አንቀው ይዘዋት ነበር።
መጸዳጃ ቤት የሌላቸው፣ የውኃ ፍሳሽ እና የቆሻሻ ማስተላለፊያ ቦይ ተደባልቀው የሚፈሱባቸው፣ ሕፃናት ቦርቀው ማደግ ቀርቶ በነጻነት አየር መተንፈስ የሚከብዳቸው አካባቢዎች የሕይወት እውነታችን ነበሩ።
ዝናብ ጠብ ባለ ቁጥር ጣሪያቸው እንደ ወንፊት የሚያፈስ፣ ነዋሪው ሌሊቱን ሙሉ ፌስታል ሲለጥፍ እና ዕቃ ሲያቀባብል ዕንቅልፍ አጥቶ የሚያድርባቸው፣ በእርጅና ስቃይ ክፉኛ የተጎሳቆሉ ጎጆዎች... አዎ፣ አዲስ አበባ እንዲህ ዓይነት መሪር ሸክም ተሸክማ፣ ግን ደግሞ የረጅም ዘመን ታሪክ ስታወራ የኖረች ከተማ ነበረች።
ነገር ግን፣ ባለፉት አምስት ዓመታት የዚህች ከተማ ታሪክ በአስደናቂ እና በማይቀለበስ ሁኔታ ተቀየረ። ከተማዋ ከረጅም የቸልተኝነት እና የድንዛዜ ዕንቅልፏ በአንድ ጊዜ ባነነች። በመደመር አስተሳሰብ በተቃኙ፣ በቀን 24 ሰዓት በሳምንት 7 ቀናት (24/7) ያለ እረፍት በሚሠሩ፣ እንደ ንብ በሚተጉ ትጉህ መሪዎች እና እጆች፣ የከተማዋ ዕጣ ፈንታ አዲስ ምዕራፍ ጀመረ።
የለውጡ መንግሥት ባመጣው የሥራ ባሕል፣ አዲስ አበባ ያን ያረጀ እና ያፈጀ የተጎሳቆለ ቆዳዋን እንደ እባብ ገፈፈችው። ዛሬ ላይ የድሮዋን ከተማ ፈልጎ ማግኘት ይከብዳል። ቆዳዋን ቀይራ፣ ፊቷን ታጥባ፣ ጸዳሏ እንደ ደመቀ ሕፃን ልጅ፣ አልያም በንጋት ጤዛ እንደፈካች ማራኪ አበባ ትፍለቀለቃለች።
ያረጀው እና ያፈጀው ፈርሶ በአዲስ ሲተካ፣ ጠባቡ ሰፍቶ የብርሃን እና የአረንጓዴ ኮሪደር ሲሆን፣ አዲስ አበባ የዘመናችን አስደናቂ የትራንስፎርሜሽን ትዕይንት ሆናለች።
ይህ የውበት እና የመሠረተ ልማት ትንሣኤ፣ አዲስ አበባን ከዓለም አቀፍ መንገደኞች ጊዜያዊ መሸጋገሪያነት አላቆ፣ ራሷን የቻለች ግዙፍ የቱሪዝም መዳረሻ አድርጓታል።
በተለይም ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን፣ ኮንፈረንሶችን እና ኤግዚቢሽኖችን (የማይስ - MICE ቱሪዝም) በብቃት በማስተናገድ ረገድ፣ የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን በኮንክሪት እና በውበት አስደግፋ በተግባር እያረጋገጠች ትገኛለች።
ይሁን እንጂ፣ የዚህች ከተማ ዳግም መፈጠር አስደናቂነቱ ያለው ውበቷ፣ የመንገዶቿ ስፋት ወይም የሕንፃዎቿ ከፍታ ላይ ብቻ አይደለም። የአዲስ አበባ ትልቁ እና ታሪካዊው ስኬት "ርኅሩኅ ነፍስ" መላበሷ ነው። በዓለም ላይ ያሉ ብዙ ዘመናዊ ከተሞች ሲገነቡ፣ ዝቅተኛ ገቢ ያለውን ማኅበረሰብ እንደ ቆሻሻ ጠርገው ወደ ዳር በማውጣት ነው። የኛዋ አዲስ አበባ ግን ድሆችን የምትገፋ የሲሚንቶ ጫካ ሳትሆን፣ ዜጎቿን በዕቅፏ የምታስጠልል እና የምታሞቅ ርኅሩኅ እናት ሆናለች።
አቅመ ደካማ ዜጎች በክረምት ብርድ እና ዝናብ እንዳይሠቃዩ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የተጎሳቆሉ ቤቶቻቸው በአዲስ መልክ ታድሰውላቸዋል፤ ሰብዓዊ ክብር በሚመጥን መልኩ ተሠርተው በነጻ ተሰጥተዋቸዋል።
ከዚህም በላይ፣ የነገ ሀገር ተረካቢ ሕፃናት በረኃብ አለንጋ እንዳይገረፉ፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች በትምህርት ቤቶች ውስጥ በየቀኑ የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ ተደርጓል።
ማዕድ በማጋራት፣ የምገባ ማዕከላትን በማስፋፋት እና የሌማት ትሩፋት ፕሮግራሞችን ተግባራዊ በማድረግ፣ አስተዳደሩ ማኅበራዊ ፍትሕን በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል። የከተማዋ ዕድገት የነዋሪዎቿን ዕንባ እያበሰ፣ ዝቅተኛውን የኅብረተሰብ ክፍል በጥብቅ የምትደግፍ የዘላቂ ብልጽግና ተምሳሌት አድርጓታል።
በአጠቃላይ ሲታይ፣ የአዲስ አበባ የአምስት ዓመታት የልማት ዕርምጃ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከውድቀት ወደ ትንሣኤ፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን የተደረገ የሥልጣኔ ሽግግር ነው።
የከተማዋ ሁለንተናዊ ዕድገት፣ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን መላው አፍሪካ የሚኮራባት፣ ስሟን እና ግብሯን ያስተሳሰረች "ስማርት ከተማ" አድርጓታል። አዲስ አበባ ዛሬ በእርግጥም አዲስ ናት፤ በእርግጥም እንደ ስሟ ደምቃ አብባለች!
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: