የአፍሪካ የዲፕሎማሲ መዲና አዲስ አበባ ለዐሥርት ዓመታት አሮጌ እና የተፋፈጉ ሰፈሮች የበዙባት ሆና የቆየች ቢሆንም፣ ላለፉት አምስት ዓመታት በተካሄደው የተቀናጀ የመልሶ ማልማት ሥራ የተጎሳቆሉ አካባቢዎቿ ስብስብ ከ74 በመቶ ወደ 30 በመቶ ዝቅ ብሏል።
ይህ ስኬት እንደ ፒያሳ፣ መርካቶ፣ ልደታ፣ ሰንጋተራ እና ቂርቆስ ባሉ ነባር ስፍራዎች በተተገበሩ ፕሮጀክቶች የተረጋገጠ ሲሆን፣ ቀደም ሲል የቆሻሻ መጣያ የነበሩት የወንዞች ዳርቻዎችም በሸገር እና ቀበና ፕሮጀክቶች አማካኝነት የውበት እና የመዝናኛ ፓርኮች ሆነዋል።
የመዲናዋ የኮሪደር ልማት የእግር መንገድ፣ የሳይክል መስመር እና የመኪና ማቆሚያዎችን በመገንባት የእግረኛውን ደኅንነት ማረጋገጥ አስችሏል።
ከሜክሲኮ እስከ ለገሀር ባለው መስመር 2 ሺህ 145 ተሽከርካሪዎችን እና ከ1 ሺህ 600 በላይ ታክሲ እና አውቶብሶችን ማስተናገድ የሚችሉ ዘመናዊ ተርሚናሎች ለአገልግሎት በቅተዋል።
የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያዎች ቁጥር ከአንድ ወደ 43 ማደጉ እንዲሁም እንደ ላፍቶ፣ ቤቴል ያሉ አራት ትልልቅ ዘመናዊ ሆስፒታሎች ወደ አገልግሎት መግባታቸው የከተማዋን የጤና እና የጽዳት ደረጃ ከፍ አድርጎታል።
አስተዳደሩ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ 6 ግዙፍ የገበያ ማዕከላት እና 250 የቅዳሜ እና እሑድ ገበያዎችን ያመቻቸ ሲሆን፣ በየዓመቱ በሚመድበው ከ18 ቢሊዮን ብር በላይ ድጎማ በትምህርት ቤት ምገባ፣ በወል ትራንስፖርት እና በጤና መድኅን የዜጎችን ማኅበራዊ ፍትሕ እያረጋገጠ ይገኛል።
አዲስ አበባ የመፈናቀል እና የካሳ አሰጣጥ ተግዳሮቶችን በፍትሐዊነት በመፍታት ለነዋሪዎቿ ምቹ እና ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ተመራጭ ሜትሮፖሊታን ከተማ በመሆን የብልጽግና ተምሳሌትነቷን አረጋግጣለች።
በሰለሞን ገዳ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: